ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጪ ባንኮች አምስት ቢሊዮን ብር ዝቅተኛ ካፒታል ሟሟላት እንደሚኖርባቸው ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው አዲስ መመሪያ ጥብቅ ቅደመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠ ነው ተብሏል።
መመሪያው በባንኩ ዘርፍ የውጭ ሀገራት ተሳትፎን የውጭ ባንክ ተቀጥላ፣ የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ እና የእንደራሴ ቢሮ ብሎ የሚከፍል ሲሆን ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የወንጀል እና የታክስ ማጣራትን ጨምሮ ጥብቅ ምርምራዎችን ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው አስቀምጧል።
የውጭ ባንኮች የደንበኞቻቸውን መረጃ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ብቻ ለማስቀመጥ እና ለመጠቀም ይገደዳሉ የተባለ ሲሆን ክፍያን በተመለከተ ከውጭ የሚገቡ ባንኮች ለምርመራ 200 ሺህ፣ ለፈቃድ 400 ሺህ እና ለእድሳት 400 ሺህ ብር መክፈል እንዳለባቸው ተቀምጧል።
መመሪያው የሀገር ውስጥ ባንኮች ካፒታላቸውን መጨመር፣ የመረጃ አጠቃቀም ሕጋቸውን ከሀገሪቱ ጋር ማስማማት እና በቦርዶቻቸው ውስጥ የፆታ ብዝሃነትን ማረጋገጥ ጨምሮ ደረጃቻውን ከፍ እንዲያደርጉም ደንግጓል።
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች አምስት የሚደርሱ የባንክ ፈቃድ ለመስጠት ማቀዷን ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ በወቅቱ እንዳሉት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባንኮች እና ባለሀብቶች የባንክ ፈቃድ እንደሚሰጥ ተናግረው ነበር፡፡
ይህም የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ አገልግሎት ለውጭ ተፎካካሪዎች ክፍት ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እስካሁን የኢትዮጵያ ባንክ ዘርፍ ለውጭ አገራት ባንኮች ዝግ ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ግን ለውጭ አገራት ተፎካካሪዎች ክፍት ይደረጋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የውጭ ባለሀብቶች በባንክ ኢንዱስትሪ ዘርፉም ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በጋራ የሚሰሩበት አማራጭ ሊኖር እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
ዋና መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው ስታንዳርድ ባንክ በአፍሪካ ትልቁን ያልተነካ ገበያ እየፈለገ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት የባንክ ፍቃድ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከሁለት ሳምንት በኃላ የኢንቨስትመንት የባንክ ፍቃድ ማመልከቻዎችን እንደሚቀበል ከቀናት በፊት መግለፁ አይዘነጋም ።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የሞሮኮ፣ የኬንያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባንኮች በኢትዮጵያ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ ማሞ ምህረቱ ባሳፍነው ሕዳር ወር ላይ ተናግረው ነበር፡፡
የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በባንክ፣ በቴሌኮም፣ በትራንስፖርት እና አቬሽን ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩ ቆይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ ተደርገው የቆዩ ዘርፎች ክፍት እንደሚደረጉ ቃል የገቡ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የውጭ ቴሌኮም ፈቃድ ማግኘቱም ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም የመንግሥት የልማት ድርጅት እና ብቸኛ የቴሌኮም ድርጅት ሆኖ የቆየውን የኢትዮ ቴሌኮም 45 በመቶ ድርሻ ለውጭ ባለሀብት በመሸጥ ሦስተኛ የውጭ ቴሌኮም ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ቢወጣም ተወዳዳሪ በመጥፋቱ ጨረታው ቀርቷል፡፡