ኢትዮጵያ ለቤት ሰራተኞች የጡረታ ክፍያ ልትጀምር ነው

የቤት ሠራተኞችን የጡረታ ተጠቃሚ የሚያደርግ የሥራ ቅጥር ውልና አጠቃላይ ደንብ በ6 ወር ውስጥ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ

የቤት ሠራተኞች ጡረታን ጨምሮ የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የሥራ ቅጥር ውልና አጠቃላይ የቤት ሠራተኞች ደንብ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አንድነት የኢትዮጵያ የቤት ውስጥ ሠራተኞች ማህበራት ሕብረት አስታውቋል።

የሕብረቱ ፕሬዚዳንት ሂሩት አበራ የቤት ሠራተኞችን ሕግ በሚመለከት በዓለም አቀፉ ኮንቬንሽን 189 በተቀመጠው ሕግ መሠረት በቀጥታ ለመተግበር አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ፤ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲስማማ ተደርጎ ደንቡና የሥራ ቅጥር ውሉ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

ይኸው ደንብ በረቂቅ ደረጃ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ጨምረው አስታውቀዋል።

ለአብነትም በቋሚነት የሚሰሩ ሠራተኞች በሥራ ቦታቸው ላይ የመኖር፣ ተመላላሽ የሆኑት ደግሞ ሰርተው የሚሄዱበትን አግባብ የለየና የሥራ ቅጥር ውሉን ጨምሮ የሚወጣው ደንብ መሠረታዊ የሆኑ መብቶቻቸው ላይ ያተኮረ መሆኑን የሕብረቱ ፕሬዝደንት ለአሃዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የሥራ ቅጥር ውሎች መኖራቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፤ ነገር ግን ውሎቹ ሕጋዊ አለመሆናቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም በመነሳት ለቀጣሪዎችም ሆነ ለቤት ሠራተኞች የሚጠቅም ወጥ የሆነ የሥራ መቀጠሪያ ውል እንዲኖር ለማስቻል ያሰበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚሁጋ ተያይዞም ውሉ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ‘ተፈፃሚነቱስ እስከምን ድረስ ነው?’ የሚለውን ጉዳይ ማህበረሰቡ በደንብ ማየት ስላለበት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቤት ሠራተኞች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ዘርፈ ብዙ እንደሆኑ የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፤ የሥራ ቅጥር ውሉን ጨምሮ አጠቃላይ የቤት ሠራተኞች የሕግ ማዕቀፍ ጸድቆ ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሁሉ ሊቀርፍ እንደሚችል አንስተዋል።

አክለውም “ውሉ ለቤት ሠራተኝነት ሥራ እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ የሕክምና አገልግሎት፣ ሰርተው ሲደክማቸው በጡረታ የሚካተቱበት አግባብን ጨምሮ ማህበራዊ ዋስትናቸውን ሊያረጋግጡ የሚችሉበትን መንገድ ይፈጥራል” ብለዋል።

በመሆኑም በዚህ 6 ወር ጊዜ ውስጥ የሥራ ቅጥር ውሉና አጠቃላይ የቤት ሠራተኞች ደንብ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች ቅጥር የተለመደ ሲሆን እነዚህ ሰራተኞች አነስተኛ ወርሃዊ ደመወዝ፣ የጉልበት ብዝበዛ፣ ጾታዊ ትንኮሳ እና ሌሎች ጉዳቶችን ያስተናግዳሉ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ግን በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያዊን የቤት ውስጥ አገልግሎቶችን ለመስጠት በሚል ወደ መካከለኛው መስራቅ ሀገራት እንደሚያቀኑ የዓለም ስራ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *