በኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ 1ሺህ 500 ሰዎች በውሾች ተነክሰዋል ተብሏል
ራቢስ በተሰኘ ቫይረስ አማካኝነት በሚከሰተው የእብድ ውሻ በሽታ የተነሳ ባለፋት ስምንት ወራት በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ የ18 ሰዎች ህይወት ማለፋን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
በኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዲቪዥን ክፍል ተመራማሪ አቶ መስፍን አክሊሉ እንደተናገሩት እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የውሾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
በተለይም ደግሞ ባለቤት አልባ ውሾችን በማስወገድ በኩል በቂ ስራ ባለመሰራቱ ሁኔታውን እንዲባባስ አድርጓል።ባለፋት ስምንት ወራት በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ 1462 ሰዎች የውሻ ንክሻ እንዳጋጠማቸውና ክትባት እንደወሰዱ የተናገሩት ተመራማሪው በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን ይህን በሽታ ለመግታት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከእነዚህም መካከል 1050ዎቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሲሆኑ 412 የሚሆኑት ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጪ እንደሆኑ ተጠቅሷል።በተጨማሪም የመከላከያ ክትባት ሳይወስዱ ህይወታቸው ካለፋት ሰዎች ውስጥ አራቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሆኑ ተመራማሪው ተናግረው ቀሪዎቹ 14ቱ ከአዲስ አበባ ውጪ እንደሆኑ አንስተዋል።
አብዛኛዎቹ የእብድ ውሻ በሽታዎች መንስኤያቸው የውሻ ንክሻ እንደመሆኑ በሽታውን ለመከላከል ውሾችን በየጊዜው ከማስከተብ ባለፈ በጤና ማዕከላት የሚሰጠውን ክትባትና ሕክምና በጊዜ መውሰድ የሚገባ በመሆኑ በአዲስ አበባ የተጀመረውን ይህንን ተግባር ወደ ሌሎች ክልሎች ለማስፋፋት ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በእብድ ውሻ ንክሻ ወይም በሌሎች በተለከፉ እንስሳት የእብድ ውሻ በሽታ ወደ ሰዎች ሊተላለፍ ይችላል።
ይህም በበሽታው የተበከለ እንስሳ ሌላ እንስሳ ወይም ሰው ሲቧጭር አሊያም ሲናከስ የእብድ ውሻ በሽታን ሊያስተላለፍ እንደሚችል ሲነገር ምልክቶቹ ከታዩ በኋላ የእብድ ውሻ በሽታ በአብዛኛው ሞትን ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል።
የእብድ ውሻ በሽታ በየዓመቱ ከ2700 በላይ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገድል የግብርና ሚኒስቴር ከአንድ ዓመት በፊት ያወጣው ሪፖርት ያስረዳል፡፡
የግብርና ሚንስቴር እንደገለጸው በኢትዮጵያ የእብድ ውሻ በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሳ እና ስጋት እየሆነ በመምጣቱ በዓመት እስከ 2 ሺህ 7 መቶ የሚደርሱ ሰዎች ይሞታሉ።
በሚኒስቴሩ የእንስሳት ጤናና ፐብሊክ ሄልዝ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ውብሸት ዘውዴ በወቅቱ እንደተናገሩት ሁኔታው አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልል ከተሞች ትልቅ ስጋት ሆኗል፡፡
በከተሞች አካባቢ ባለቤት አልባ ውሾች በየመንገዱና በየጎዳናው የሚስተዋሉ በመሆናቸው በርካታ ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ ተጠቂ እየሆኑ ነው ተብሏል።
በሽታውን ለመከላከል እስከ 70 በመቶ የሚደርሱ ውሾች ቢከተቡ በሽታው ከውሻው ወደ ሰዎች እንዳይተላለፍ ማድረግ እንደሚቻልም ተገልጿል።
አስቀድሞ በሽታው በሰዎች ህይወትና ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ኢትዮጵያ የአንድ ጤና ዘዴ (One Health) በመጠቀም በ2030 የውሻ በሽታን ለማስወገድና ለመቆጣጠር የተለያዩ ስልቶችን ቀይሳ እየሰራች ትገኛለች ተብሏል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የእብድ ውሻን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከል ከ347 ሺ በላይ ውሾች ተከትበዋል ተብሏል።
የእብድ ውሻ በሽታ በዓለማችን ከአንታርክቲካ በስተቀር በሁሉም አህጉር እንደሚከሰት የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
እስያ እና አፍሪካ የእብድ ውሻ በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያለባቸው አህጉራት ሲሆኑ ምዕራብ አውሮፓ፣ ሲንጋፖር እና ኒውዝላንድ ደግሞ የእብድ ውሻ በሽታ ስጋት የሌለባቸው ሀገራት ናቸው።