ኤርትራዊያንን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መኪና ሲያጓጉዙ የተገኙ ወታደሮች በእስራት ተቀጡ

በሰዎች ዝውውር የተከሰሱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በእሥራት ተቀጥተዋል።

በህገ ወጥ የሠዎች ዝውውር ተሠማርተዋል የተባሉ አንድ ከፍተኛ የአገር መከላከያ ሠራዊት አዛዥን ጨምሮ ሁለት የሠራዊቱ አባላት በ8 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡

አባላቱ ቅጣቱ የተላለፈባቸው ትናንት በአርባምንጭ ከተማ በተሰየመው የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባሳለፈው የፍርድ ውሳኔ ነው  ተብሏል፡፡

ቅጣቱ የተወሰነው በሠራዊቱ የደቡብ ዕዝ 202ኛ ኮር 1ኛ ሬጅመንት አዛዥ ሻምበል መብራቱ ታዴ እና በሬጅመንቱ የኦራል አሽከርካሪ በሆነው ወታደር ጌታቸው ክብረት በተባሉት  ላይ እንደሆነ ዶቸቪሌ ዘግቧል።

አዛዡ እና የሰራዊቱ አባል ቅጣቱ የተወሰነባቸው ህዳር 16 2016 ዓ.ም 52 ኤርትራዊያንን በሠራዊቱ የኦራል ተሽከርካሪ በመጫን ወደ ኬኒያ በማሻገር ላይ እንዳሉ በመያዛቸው መሆኑን የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ  ሽመልስ ጮራ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

የፌደራል ፍትህ ሚኒስቴር ዐቃቤ ህግ ክሱ በውክልና በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲታይለት ባቀረበው የክስ መዝገብ መሰረት የተከሳሾቹን ጉዳይ ሲመለከት መቆየቱን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ “ ተከሳሾቹ የሰዎች ዝውውር ወንጀሉን የፈጸሙት ለግዳጅ የተሠጣቸውና የሠሌዳ ቁጥሩ መከ ኮድ  2-2347  የሆነ ኦራል ተሽከርካሪን በመጠቀም ነው ፡፡ ሰዎቹን በመጓጓዝ ላይ እንዳሉ የተያዙትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሌ ዞን ቀርቀርቴ በተባለ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው ፡፡

ተከሳሾቹ  በፎቶ ፣ በሰነድ አና በሰው ምስክር የቀረበባቸውን ክስ ሊያሰተባብሉ አልቻሉም።

ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው በ8 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት እና እንዲሁም በ10,000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑም ተገልጿል።

በርካታ ኤርትራዊያን ስደተኞች በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የሚጠለሉ ሲሆን ስደተኞቹ ወደ ሌሎች ሀገራት ለመሸጋገር ኢትዮጵያን ይጠቀማሉ፡፡

እንደ ተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ሪፖርት ከሆነ 200 ሺህ ገደማ ኤርትራዊያን ስደተኞች በኢትዮጵያ ይኖራሉ፡፡

ተቋሙ ኢትዮጵያ የተጠለሉ ኤርትራዊያን ስደተኞችን በግድ ወደ ሀገራቸው እየመለሰች ነው ሲል ከሶስት ወራት በፊት አስታውቆ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በበኩሏ በርካታ ኤርትራዊያን ስደተኞች አሁንም የመኖሪያ ፈቃድ መስጠቷን እና በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉ ገልጻ በሀይል ወደ አገራቸው ተመልሰዋል በሚል የተነሳውን ቅሬታ ሀሰተኛ መሆኑን አስታውቃለች፡፡

በ2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነበር ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ያደሱት፡፡

ሁለቱ ሀገራት የመደበኛ የስልክ አገልግሎትን ካስጀመሩ ከሰባት ዓመታት በኋላ ባሳለፍነው ህዳር ወር ላይ ዳግም ተቋርጧል፡፡

ይህን ተከትሎም ከሐምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የስልክ አገልግሎት ሲሰራ የነበረ ሲሆን ከመስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደተቋረጠ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነሀሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ማቆሙ ይታወሳል፡፡

ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ እና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጫለሁ ያለው አየር መንገዱ በኤርትራ ያለው አሰራር አስቸጋሪ እና ከቁጥጥሩ ውጪ መሆኑ ለበረራው መቋረጥ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

ኤርትራ በኢትዮጵያ የተለያዩ ትንኮሳዎች እየተፈጸሙባት እንደሆነ በተደጋጋሚ የገለጸች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ መንገድ ወደብ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥልበት ባሳለፍነው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የመንግስታቸውን የስድስት ወራት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *