የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥበበ ግዮን ግቢ ስፔሻላንስድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም ዳኘ በተተኮሰባቸው ጥይት መገዳላቸውን ተገልጿል፡፡
በአማራ ክልል የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥበበ ግዮን ግቢ ስፔሻላንስድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም ዳኘ በተተኮሰባቸው ጥይት መገዳላቸውን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ ከመነገር ይቆይ ያሉ አንድ የዩኒቨርሲቲው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሰራተኛ እንዳሉት “ዶክተር አንዷለም መኪናው ውስጥ በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ ተገኝቷል ” ሲሉ አስረድተዋል።
ተኩሱ ከመጀመሩ ከ30 ደቂቃዎች በፊት በአካባቢው እንዳለፉ የገለጹት እኝሁ አካል ስለ ዶክተር አንዷለም ሲገልጹ፣ “ ከሥራ እየተመለሰ በነበረበት ወቅት ቆሸ የሚባለው ሰፈር ሲደርስ ነው ጥይት የተተኮሰበት ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“ ዶክተር አንዷለምን የምናውቀው ደግ፣ ሩህሩህ፣ የሁላችንም ምሳሌ አድርገን ነው። ሰው ነው ከሰውም ሰው ” ሲሉ እያለቀሱ ተናግረዋል።
በጥበበ ግዮን ሆስፒታል ግቢ ህክምና ጤና ሳይንስ ኢንተርን ሀኪሞች በበኩላቸው፣ “ ዶክተር አንዷለም ከከተማ ከሥራ ውሎ ሲመለስ ምሽት ላይ ነው የተመታው። ግን ማን እንደመታው የተረጋገጠ ነገር የለም ” ሲሉ ተናግረዋል።
“አስከሬኑም ለፖሊስ ተደውሎ ነው ማታ የተነሳው ” ያሉት ኢንተርን ሀኪሞቹ፣ “ አሁን ሀኪሞቹም፣ ሬዚደንቶቹም ሁሉም የባሕር ዳር ዩኑቨርሲቲ ተማሪዎችና ሠራተኞች ሀዘኑን እየተካፈልን ነው ያለነው ” ብለዋል።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው ዶክተር አንዷለም ደጉ መገደላቸውን ገልጸዋል፡፡
ዶክተር አንዷለም ዳኘ የዩኒቨርሲቲው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስፔሻሊስት፤ የጉበት፣ የቆሽት፣ የሀሞት ጠጠር መስመር ሰብ ስፐረሻሊስት ሀኪም፣ እንዲሁም የልጆች አባት እንደነበር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ህክምና ተማሪዎች ማኀበር (ባሕር ዳር) “በጥይት ተገደሉ” በተባሉት በዶክተር አንዷለም ዳኘ ግድያ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጾ፤ “ከፍተኛና ልዩ ስጋት አለብን” ሲል ተናግሯል።
ማኀበሩ ይህን ያለው በኮሌጁ አካላትም ሆነ በኢንተርን ሀኪሞች የግድያና የዘረፋ ሙከራዎች እየተደረጉባቸው መሆናቸውን በመግለጽ ጭምር ነው።
“ኦፊሻል ስላልወጣ እንጂ ከሦስት ሳምንት በፊት ሥራ ስራ ቦታ ላይ የነበረ አንድ የህክምና ባለሙያ ተገድሏል በሽጉጥ ” ሲልም አስታውሷል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የባሕርዳር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊን ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ዋቢ አድርጎ “ፖሊስ ድርጊቱን ማን ፈፀመው? እንዴት ተፈፀም? የሚለውን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።