ጎንደር ዩንቨርስቲ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ 100 ሺህ ተማሪዎችን እንዳስመረቀ ተገልጿል።
ዩንቨርሲቲው በኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ዕጥረት ለመፍታት በሚል በ1947 ዓ.ም መመስረቱም ተገልጿል።
የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን እንዳሉት ዩንቨርሲቲው በ70 ዓመት ታሪኩ 100 ሺህ ተማሪዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሐኪሞች ዕጥረትን ተከትሎ የውጭ ሀገራት የህክምና ባለሙያዎች ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ ይነበረ ሲሆን ጎንደር ዩንቨርሲቲ ይህ ችግር በቋሚነት እንዲፈታ የራሱን አስተዋጽኦ መወጣቱም ተጠቅሷል።
ጎንደር ዩኒቨርስቲ ሕንፃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገነባ መሬታቸውን ለሰጡ ግለሰቦች ዕውቅና በመስጠት የአርሶ አደሮች ቀንን እሰይማለሁም ብሏል።
በተመሳሳይ በተለያየ መንገድ አሰተዋፅኦ ላደረጉለት ግለሰቦች የሕንፃ፣ የመንገድና የአዳራሽ ስያሜ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል።
ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው ስያሜው በዩኒቨርስቲውና በሆስፒታሉ ታሪክ ጉልህ ድርሻ ለነበራቸው ግለሰቦች፣ ለአሁኑ ትውልድ መነሳሳትን እንዲፈጥር ታስቦ የሚፈፀም ነው ብለዋል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ አሁን ላይ በ11 ኮሌጆች በ87 የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞችና ከ300 በላይ በሁለተኛ ሦስተኛ ዲግሪና ስፔሻላይዜሽን ፕሮግራሞች ከ40 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑን አስታውቋል።
በተጨማሪም 12 የምርምር ማዕከላት እንዲሁም አንድ የማስተማሪያ ሆስፒታልና የእንስሳት ሕክምና ሆስፒታልም አለው።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ 45 የመንግስት ዩንቨርስቲዎች ያሉ ሲሆን አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩንቨርስቲ ሆኗል።
የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመት እያከበረ ባለው ጎንደር ዩንቨርስቲ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የራስ ገዝ ዩንቨርስቲዎችን ቁጥር 10 የማድረግ እቅድ ተይዟል ብለዋል።
ከነዚህ 10 ዩንቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ይሆናል የተባለው ጎንደር ዩንቨርስቲ ነው ተብሏል።
በ1996 ዓ . ም ወደ ዩንቨርሲቲነት ያደገው ጎንደር ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሻለ አስተዋጽኦ አድርገዋል ለተባሉ 10 ሰዎች የክብር ዶክትሬት መስጠቱንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።