ሀገሪቱ ለ20 የውጭ ዜግነት ለነበራቸው ሰዎች የኢትዮጵየዊ ዜግነት ሰጥታለች ተብሏል
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው ላይ እንዳሉት ለ14 ሺህ 367 ለሚሆኑ የውጭ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለ20 ግለሰቦች ደግሞ የኢትዮጵያዊ ዜግነት እንደተሰጣቸውም ወይዘሮ ሰላማዊት በመግለጫው ለይ ጠቅሰዋል።
ተቋሙ ለዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሠው ሀይሉን የማጠናከር፤ አሰራሩን በቴክኖሎጂ የማገዝ ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ለጉብኝት ቱሪስት፣ ለኮንፍረንስና ለቢዝነስ የሚገቡትን ለማስተናገድ በ188 ሀገራት ቪዛ ኦን አራይቫል በመክፈት እየተሰራ መሆኑም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአየር ትራንስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ እንደወጡ በመግለጫው ላይ ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ገቢ እና ወጪ መንገደኞች አገልግሎት ተሰጥቷል ተብሏል፡፡
ተቋሙ በዚሁ በተጠቀሱት ጊዜያት ውስጥ ከ721 ሺህ በላይ ፓስፖርቶችን አትሜያለሁ ያለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 98 በመቶው ለተገልጋዮች መሰጠቱ ተገልጿል።
ባለፉት ስድስት ወራት 16 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቤያለሁ ያለው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሀሰተኛ የጉዞ ሰነድ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ከ13 ሺህ በላይ ዜጎች ላይ አሰተዳደራዊ ርምጃ ወስጃለሁም ብሏል፡፡
ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ከመከላከል ረገድም ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በቅንጅት በተሰራው ስራም በሕገ-ወጥ የድለላ ሥራዎች በተለያየ የማጭበርበርና የማታለል ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ አጠቃላይ 126 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡