የቻይና ኩባንያዎች ከ300 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን የስራ እድል ፈጥረዋል ተባለ

ኢትዮጵያ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከሳበችው ውስጥ ግማሹ በቻይናዊን የተያዘ እንደሆነ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከቻይና ንግድ ምክር ቤት እና ከቻይና ኢምባሲ ጋር በአዲ አበባ ተወያይተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በዚህ ጊዜ እንደገለጸው ባለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ ከተጀመሩ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 50 በመቶ የሚሆኑት በቻይና ባለሀብቶች የለሙ ናቸው፡፡

ውይይቱ የቻይና ባለሀብቶችን ለማበረታታት የተዘጋጀ ሲሆን ውይይቱ ለቻይና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢን ለመፍጠር እና ተጨማሪ ባለሀበቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

አሁን ላይ ቻይና በኢትዮጵያ ከ 3 ሺህ 300 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀከቶችን በማልማት ላይ ናት የተባለ ሲሆን ቻይና በኢትዮጵያ ከ325 ሺህ በላይ ለሆኑ ኢትዮጵያዊያን የስራ እድሎች ፈጥራለችም ተብሏል፡፡

ከሶስት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች በሙስና እና እንግልት ምክንያት ወደ ጎረቤት ሀገራት እየተሰደዱ ነው መባሉ ይታወሳል፡፡ 

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት የቻይና ባለሃብቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠማቸው በመንግስት አመቺ የስራ ሁኔታዎች እየተሰጠ ባለመሆኑ ወደ ጎሮቤት ሃገራት ማለትም ወደ ኬንያ ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም ታንዛኒያ እያማተሩ እንደሚገኙ በወቅቱ ካፒታል ጋዜጣ ዘግቦ ነበር።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ተወካይ እንደተናገሩት በብዙ ምክንያቶች ቻይናውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ንግዳቸውን ወደ ጎሮቤት አገሮች አዙረዋል ።

“ይህ ለኤምባሲው ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ትልቅ ስጋት ነዉ ምክንያቱም የእኛ ተልዕኮ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለዉን ትብብር ማመቻቸት እንደመሆኑ ይህ ደግሞ በተለይ ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ ትልቅ ስጋት ነዉ” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶች ተወካይ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና እንዳለባት አረጋግጠዋል።

የመጀመሪያው የደህንነት ቀውስ፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እና እንዲሁም ግብይት ስርዓት እየጠበበ መምጣቱ ዋነኛው ምክንያቶች እንደሆኑ አስረድተዋል።

ከግብር ጋር በተያያዘ ደግሞ ባለሀብቶች የሚያጋጥሟቸው ሌላኛዉ ችግር መሆኑን ያነሱ ሲሆን ሁል ጊዜ “ከጉምሩክ ቢሮ ጋር በተያያዘ የሚመጣው ቀረጥ” ከባድ አድርጎታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ እንዳስታወቀው ቻይናውያን ባለሃብቶች በመሰረተ ልማት ግንባታ  ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ኩባንያዎች በመክፈት ለራሳቸው ገንዘብ እያፈሩ ለኢትዮጵያ ዘመናዊነት ደግሞ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *