ኢትዮጵያ በሕክምና ባለሙያዎች የታገዘ ሞት እንዲፈጸም ፈቀደች

ከወራት በፊት በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት የተዘጋጀው “የጤና አገልግሎት አስተዳደር አዋጅ” በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል፡፡

ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ ያልተለመዱ እና አዳዲስ የጤና አገልግሎቶች ለዜጎች እንዲሰጡ ይፈቅዳል፡፡

ለአብነትም በተፈጥሯዊ መንገድ ልጅ መውለድ ላልቻሉ ባለትዳሮች በቴክኖሎጂ የታገዘ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚለው አንዱ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አተነፋፈሳቸው በመሳሪያ ላይ ብቻ የተመሰረተ ሰዎች ህይወታቸው ስለሚቋረጥበት ሁኔታም በአዋጁ ላይ ተደንግጓል፡፡

በዚህ አዋጅ መሰረትም በመሳሪያ ላይ ብቻ የተመሰረተ የአተነፋፈስ ስርዓትን እንዲቋረጥ የሚፈቅድ ሲሆን ይህም የሚቻለው የልብ እና የመተንፈሻ አካላት የአሰራር ሥርዓት መመለስ በማይቻልበት ደረጃ ሥራቸውን ሲያቆሙ ወይም የአንጎል ሞት ሲረጋገጥ ብቻ ነው።

የዚህ ስርዓት አተገባበር መመሪያን በቀጣይ የጤና ሚኒስቴር እንደሚያወጣ የተገለጸ ሲሆን ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ በማይድን ህመም የሚሰቃዩ ዜጎችን ለመርዳት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በአፍሪካ እንዲህ አይነት ህግ ሲወጣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በአውሮፓ እና አሜሪካ ሀገራት ግን መተግበር ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ሌላኛው በዚህ አዋጅ ላይ የተደነገገው በጎ ፈቃደኞች የዘር ፍሬያቸውን እንዲለግሱ የሚፈቅደው ሲሆን  “ፈቃድ የተሰጠው የጤና ተቋም በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ ተዋልዶ የሕክምና አገልገሎት ሊሰጥ ይችላል” ሲል ሕክምናው በሕግ መፈቀዱን ተደንግጓል።

ሌላኛው በዚህ አዋጅ ላይ የተፈቀደው የሰውነት አካል ልገሳ ጉዳይ ሲሆን በጎ ፈቃደኞች በራሳቸው ጤና ላይ ለህይወታቸው አስጊ ባልሆነ መንገድ መለገስ እንደሚችሉ በአዋጁ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በዚህ አዋጅ ላይ ከተካተቱት ጉዳዮች መካከልም ሞቶ የተገኘ የሰው አስከሬን ለምርምር ስራ እንዲውል ፈቅዷል፡፡

አስከሬንን ለማስተማሪያነት ወይም ለምርምር ማዘጋጀት የሚችለው አግባብነት ባለው አካል የተመረጠ የጤና ተቋም ነው እንደሆነም በአዋጁ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ማንኛውም አስክሬንን ለማስተማሪያነት ወይም ለምርምር እንዲያዘጋጅ የተመረጠ ተቋም ያዘጋጀውን አስክሬን ከሌላ የማስተማሪያ እና የምርምር ተቋም ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሰረት አስክሬንን ለማስተማሪያነት እና ለምርምር ተግባር እንዲውልም ይፈቅዳል፡፡

አስከሬንን ለትምህርት እና ምርምር እነማን መጠቀም የሚቻለው እንዴት እና መቼ ነው? ለሚለው ሟቹ በሕይወት በነበረበት ወቅት አግባብ ባለው አካል ፊት ሙሉ ሰውነቱን ለመለገስ ፈቃዱን ሰጥቶ ከሆነ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪም የሟቹ የቅርብ ዘመድ ቀርቦ አስክሬኑን ለመውሰድ በሰባት ቀናት ውስጥ ካልጠየቀ ጉዳዩ የሚመለከተውን የመንግስት አካል በማሳወቅ አስከሬንን ለትምህርት ወይም ለምርምር አገልግሎት መጠቀም ይችላል ተብሏል፡፡

ይሁንና ከላይ የተጠቀሱት እንዳሉ ሆኖ አስከሬኑ ለምርምር ወይም ለተማሪዎች የተግባር ልምምድ በመዘጋጀት ላይ ባለበት ወቅት የቅርብ ዘመዱ አስክሬኑን ለመውሰድ ከጠየቀ የመውሰድ መብት እንዳለው ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *