በሀዋሳ አቅራቢያ በተከሰተ የትራፊክ አደጋ ሙሽራውን ጨምሮ 74 ሰዎች ሞተዋል።
በትናንትናው ዕለት በሲዳማ ክልል፣ ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ቦና ወረዳ ልዩ ስሙ ጋላና ድልድይ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ ሰርገኞችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አይሱዙ መኪና ተገልብጦ ሙሽራውን ጨምሮ የ74 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
የምስራቃዊ ሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ ማቴ መንገሻ (ዶ/ር) እንዳሉት “አይሱዚው 11 ሰዓት አካባቢ መነሻዉን ቦና ወረዳ ሚሪዴ ገጠር ቀበሌ አድርጎ ወራንቻ ወደተባለ አጎራበች ቀበሌ የወንድ ወገን የሆኑ ከ70 በላይ ሰርገኞችን ጭኖ ወደ ሴቷ ቤት ጉዞ ላይ ነበር ” ብለዋል።
ገላና ድልድይ ላይ ሲደርስ ግን ድልድዩን ስቶ ወደ ወንዝ ዉስጥ በመግባቱ እስካሁን በተጣራዉ በአጠቃላይ የ74 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።
በ4 ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንና አንዲት ሴት ወደ ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል መላኳንም ማቴ (ዶ/ር) ጨምረው ገልፀዋል።
የአደጋው ትክክለኛ መንስኤ እየተጣራ ነዉ ያሉት ሀላፊው “በገጠር አካባቢ በሰርግ እና ደስታ ወቅት በክፍት መኪኖች ላይ ከመጠን በላይ መጫንና አልፎ አልፎም መጠጥ የመቀማመስ ሁኔታዎች ስለሚኖሩ፤ ይህ ለአደጋው አንዱ መንስዔ ተደርጎ ይገመታል” ብለዋል።
የክልሉ ፖሊስ መኪናው ላይ የነበሩት ወገኖች በቡና እርሻ ስራ የተሰማሩ እና ህይወታቸውም በዚህ ስራ የሚተዳደሩ መሆናቸውንም አስታውቋል።
አደጋው ወንዱ ሙሽራ ወደ ሴቷ ቤት ለመሄድ በጉዞ ላይ እያለ ሲሆን ሙሽሪት ባሏን ለማግባት እየተጠባበቀች ነበር ተብሏል፡፡
በአደጋዉ የሞቱት ሁሉም ሰዎች እድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች ሲሆኑ ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ እስከ 4 ሰዉ የሞተባቸው አሉም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ከሆነባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነች፡፡
በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሲሞቱ አነስተኛ መኪና ቁጥር ባለባት ኢትዮጵያ ደግሞ ከ4 ሺህ 500 በላይ ዜጎች እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።