ሚዲያው እንደገለጸው ከህገወጥ የወርቅ ማውጣት ሂደት ጋር በተያያዘ መረጃ በማሰባሰብ ላይ የነበሩ ጋዜጤኞቹ በታጣቂዎች ታግተው ተወስደዋል።
በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን ያለውን ህገወጥ የወርቅ ማዕድን የማውጣት ሂደትና የጎንዮሽ ጉዳቶቹ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ዘገባ ለመስራት ወደ ስፍራው ያቀናው የጋዜጠኞች ቡድን በታጣቂዎች ታግተዋል ሲል ተገልጿል።
ሶስት ባለሙያዎችን የያዘው የጋዜጠኞች ቡድኑ ታህሳስ 20 ቀን 2017 ዓ/ም ጥዋት 3 ሰዓት በአስገደ ወረዳ፣ መይሊ ከተባለው ስፍራ ወጣ ብሎ በሚገኘውን መንደር በታጣቂዎች ተይዘዋል ተብሏል።
ጋዜጠኞቹ ላለፉት ሶስት ቀናት በቦታው ተገኝተው ስላለው ነገር ከአካባቢው ነዋሪዎች መረጃዎችን ሲያሰባስቡ የቆዩ ሲሆን በተለይም በመይሊ አካባቢ ማዕድናቱን ለማውጣት በጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ የተለያዩ ጎጂ ኬሚካሎች እያደረሱት ያለውን ጉዳት በተመለከተ መረጃዎች እየሰበሰቡ ነበርም የተባለ ቢሆንም በመሀል ግን በታጣቂዎቹ ስራቸውን እንዲያቋርጡ እና እንደታገቱ ጣብያው አስታውቋል።
የጋዜጠኞቹን ደህንነት ለማረጋገጥና ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የገለፀው ትግራይ ቴሌቪዥን ነገር ግን ከረፋድ 4 ሰዓት በኃላ የጋዜጠኞቹ ስልክ ዝግ በመሆኑ ምክንያት ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አለመቻሉንም አስታውቋል።
ይሁንና ቴሌቪዥን ጣቢያው ጋዜጠኞቹን አግተዋል የተባሉት ታጣቂዎችን ማንነት በይፋ አልጠቀሰም፡፡
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር እና ህወሃት መካከል አለመተማመን እና አለመግባባት ከተከሰተ ወራት አስቆጥሯል፡፡
በጊዜያዊ አስተዳድሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ እና በህወሃት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) መካከል የተከሰተው አለመተማመን ወደ ስልጣን ሽኩቻ የገባ ሲሆን አንዱ አንዱን በተለያዩ ወንጀሎች በይፋ ይከሳሉ፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ የደብረጺዮንን ቡድን ስልጣን ለመቀማት በመሞከር፣ በህገ ወጥ የማዕድናት ምዝበራ እና አመጽ ለማነሳሳት በሚል ከሰዋል፡፡
እንዲሁም የእነ ደብረጺዮን ቡድን ደግሞ የእነ ጌታቸው ረዳ ቡድን በክህደት፣ በባንዳነት እና ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ጥፋቶችን እየፈጸሙ ነው እያለ ይገኛል፡፡