የተባበሩት መንግስታ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ልዑክ (አትሚስ) የስራ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) እንዲተካው ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
ምክር ቤቱ በትላንትናው ዕለት ባደረገው ስብሰባ አልሸባብን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪዎች ከቀናት በኋላ አዲሱን ተልዕኮ እንዲጀምሩ ፈቅዷል፡፡
ውሳኔውን ለማጸደቅ ትላንት በተደረገው ድምጽ አሰጣጥ ላይ ከ15 አባል ሀገራት በ14ቱ ድጋፍ ያገኝ ሲሆን ለሰላም አስከባሪ ሀይሉ በሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ቅሬታ ያነሳቸው አሜሪካ በድምጸ ተአቅቦ ወጥታለች፡፡
ቀደም ሲል በጸደቀው የምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ መሰረት በሶማሊያ የሚሰማሩ የሰላም አስከባሪ ሀይሎችን 75 በመቶ ወጪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚሸፍን ይገልጻል፡፡
በምክር ቤቱ ድምጽ መስጠት የማይችሉት ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በመድረኩ ላይ መሳተፋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል፡፡
አዲሱ ልዑክ 11 ሺህ ሰራዊቶችን እንደሚይዝ ሲነገር እያንዳንዱ ሀገር ምን ያህል ጦር እንዳዋጣ የተባለ ነገር የለም፡፡
ግብጽ በበኩሏ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (AUSSOM) ውስጥ 5 ሺህ ጦር እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር በደረሰችው የሁለትዮሽ የመከላከያ ስምምነት ተጨማሪ የደህነንት እና ጸጥታ ስራዎችን የሚያከናውን 5 ሺህ ጦር ለመላክ ፍላጎት እንዳላት ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል፡፡
በሶማሊላንዱ የወደብ ስምምነት የተነሳ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ከሞቃዲሾ ጋር ወዳጅነቷን ያጠናከረችው ግብጽ በአዲሱ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ እንደምትሳተፍ ተረጋግጧል፡፡
በአንጻሩ ከ2007 ጀምሮ ከአሚሶም አደረጃጀት ጀምሮ በሶማሊያ ሲሳተፉ ከነበሩ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ብሩንዲ ከአዲሱ ልዑክ ራሷን ማግለሏን አስታውቃለች፡፡
ከአንካራው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ግንኙነት በኋላ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ተስማምተዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ ሁለቱ ሀገራት ባወጡት መግለጫ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እንዲሁም በጋራ ጉዳዮች ላይ አብረው እንደሚሰሩ ከመግለጽ ውጭ በአዲሱ የሰላም አስከባሪ ሀይል ውስጥ የኢትዮጵያ ጦር እንደሚሳተፍ በይፋ የተናገሩት ነገር የለም፡፡