የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረስበ ድርጅቶች ባለስልጣን በሲቪል ማህበረሰብ ስራዎች ዙሪያ የተሰማሩ ድርጅቶችን ማሸጉ ይታወሳል፡፡
ከታገዱት ድርጅቶች መካከልም “የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል” (CARD) “ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ” (AHRE) እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ባለሥልጣኑ ለድርጅቶቹን ያገደው በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ነበር፡፡
አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪው አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የጣለውን እገዳ አውግዟል፡፡
የመብቶች እና የዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኙት ድርጅቶች ላይ የተጣለው እገዳ በሲቪል ማኅበረሰቡ ምኅዳር ላይ የተቃጣው አፈና እየጨመረ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲልም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ታይግሬ ቻጉታህ እንዳሉት ድርጅቶቹ “ፖለቲካዊ ገለልተኝነት ማጣት” እና “ከብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ በመሥራት” በሚል ግልጽ እና ተጨባጭ ባልሆኑ ውንጀላዎች መታገዳቸው ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንደነዚህ ዓይነት ውንጀላዎችን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለማፈን በመሳሪያነት ሲጠቀሙበት እንደቆዩ” ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
እገዳው መጀመሪያውኑ ሊጣል የማይገባው እንደነበር የፌደራል መንግሥት የሰዎችን የመደራጀት እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶችን የሚጋፋውን ይህንን እገዳ በአስቸኳይ ሊቀለብስ እንደሚገባም አሳስበዋል።