ኢትዮጵያ ዋና መቀመጫውን ጅዳ ሳውዲ አረቢያ ካደረገው ዓለም አቀፉ የእስላማዊ ሀገራት ትብብር ድርጅት አባል ለመሆን እንቅስቃሴ መጀመሯ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ከድርጅቱ አባል ሀገራት መካከል የተወሰኑትን ድጋፍ አግኝታለችም ተብሏል፡፡
የኦርጋናይዜሽን ኦፍ እስላሚክ ኮፕሬሽን ወይም የእስላማዊ አገራት ትብብር ድርጅት 57 ሀገራትን በአባልነት የያዘ ስብስብ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የዚህ ድርጅት አባል ለመኾን ከድርጅቱ ጋር ንግግር መጀመሯን ዋዜማ ዘግቧል።
በቻዳዊው ሂሴን ብራሂም ታሃ የሚመራው ድርጅቱ በዓለም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀጥሎ በአባላት ብዛት ትልቁ የበይነ መንግሥታት ማኅበር ነው።
ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመኾን ንግግር የጀመረችው፣ ከድርጅቱ በቀረበላት ግብዣ መሠረት እንደኾነም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመኾን በጀመረችው እንቅስቃሴ የቱርክን፣ ፓኪስታንን እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶችን ድጋፍ አግኝታለች ተብሏል።
ከአፍሪካ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ናይጀሪያ ፣ቡርኪናፋሶ እና ሌሎችም የእስላማዊ አገራት ትብብር ድርጅትን ከተቀላቀሉ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ጥር ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ የእስላማዊ አገራት ትብብር ድርጅት ይህን ስምምነት እንደሚቃወም እና ከሶማሊያ ጎን እንደሚቆም መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ኢትዮጵያ በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ልምድ ያላት ሀገር ስትሆን ከአንድ ዓመት በፊት ብሪክስን መቀላቀሏ ይታወሳል፡፡
እንዲሁም ከ24 ዓመት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ትስስር ለማሳለጥ የተቋቋመው የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ጥምረትን ለመቀላቀል በሂደት ላይ እንደሆነች ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ መገለጹ ይታወሳል፡፡