በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአትክልት ምርቶች በመርከብ ለአውሮፓ ገበያ ተልከዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአትክልት ምርቶች በመርከብ ተጓጉዘው ለአውሮፓ ገበያ መላካቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ኢትዮ ቬጅ ፍሩ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በተሰኘ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራች ድርጅት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሹገር ስናብ እና ማንጄቱት የተባሉ የአትክልት ምርቶችን በመርከብ በማጓጓዝ ወደ ኔዘርላንድ መላኩ ተጠቅሷል።
በዚህም 12 ቶን ሹገር ስናብ እና ማንጄቱት የአትክልት ምርቶችን ዘመናዊ የማቀዝቀዣ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ኮንቴነር በመጠቀም ጅቡቲ ወደብ ከደረሰ በኃላ በመርከብ መላኩ ተገልጿል።
የአትክልት ምርቱ ከቆቃ ተነስቶ በመርከብ ተጓጉዞ በ23 ቀናት ውስጥ ኔዘርላድ እንደሚደርስም ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የአውሮፓ ሀገራት የኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች ዋነኛ መዳረሻ ሲሆን ከጠቅላላው የውጭ ንግድ ውስጥ የ30 በመቶ ድርሻ አለው፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ቡና፣ የአበባ ምርቶች እና ሌሎች ምርቶች ወደ አውሮፓ ከሚላኩ ምርቶች መካከል ዋነኞቹ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ ገልጸዋል።
ከተገኙ ገቢዎች መካከልም ለጎረቤት ሀገራት ከተላከ የኤሌክትሪክ ሽያጭ፣ከቡና ንግድ፣ ማዕድናት፣ከቢትኮይን ግብይት እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ ከቢትኮይን ግብይት 27 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን በአጠቃላይ ባለፉት 10 ወራት ውስጥ 55 ሚሊዮን ዶላር ከቢትኮይን ግብይት ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ፓወር (EEP) አስታውቋል፡፡
እነዚህ በአብዛኛው ከቻይና የመጡ የቢትኮይን ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ርካሽ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በመኖሩ መሆኑን አለም አቀፍ ሚድያዎች የዘገቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ፓወር ለቢትኮይን ማይኒንግ 600 ሜጋ ዋት ሀይል ዝግጁ መደረጉ ተገልጿል፡፡
በአሁን ሰአት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወነው የቢትኮይን መረታ (ቢትኮይን ማይኒንግ) ከአለም ያለው ድርሻ 2.25 ፐርሰንት ደርሷል፡፡
ይህም ኢትዮጵያን ከአሜሪካ፣ ከሆንግ ኮንግ ፣አረብ ኢምሬት እና ከሌሎች የእስያ ሀገራት በማስከተል ከፍተኛ ማይኒንግ የሚከናወንባት ሀገር አድርጓታል።
ቻይና የዛሬ ሶስት አመት የቢትኮይን ማይኒንግ መከልከሏን ተከትሎ በርካታ የሀገሪቱ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሆነ ተገልጿል።
ከሁለት ሳምንት በፊት መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የዎልስትሪቱ ቢትፉፉ የተሰኘው የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ በኢትዮጵያ መሰማራት የሚያስችለውን ሂደት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የክሪፕቶከረንሲ ግብይት ማካሄድ የሚያስችል የ80 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ሀይል መሰረት ልማት መግዛቱን ገልጿል፡፡
ቢትፉፉ የተሰኘው ይህ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኤሌክትሪክ ዋጋ ርካሽ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል፡፡