ትምህርት ሚኒስቴር ከሰዎች ለሰዎች ፋውንዴሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ከሰዎች ለሰዎች ፋውዴሽን ጋር ሦስት ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል።
የስምምነት ሰንዱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሰዎች ለሰዎች ፋውንዴሽን ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሰባስቲያን ብራንዲስ ተፈራርመዋል።
በመግባቢያ ስምምነቱም ሰዎች ለሰዎች ፋውንዴሽን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለመገንባት ካቀዳቸው 13 ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል ሦስቱን የሚገነባ መሆኑ ተጠቅሷል።
የልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ የሚካሄድው በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀው አዲስ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ዲዛይን መሰረት ነው ተብሏል፡፡
የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ሙሉ የግንባታ ወጪን በመሸፈን እንዲሁም ለመማር ማስተማር ሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን አሟልቶ ፋውንዴሽኑ የሚያስረክብ መሆኑም ተገልጿል።
እነዚህ ትምህርት ቤቶች በአፋር፣ ሶማሌ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገነቡ ሲሆን ግንባታቸውም ከ2025 እስከ 2029 እ.ኤ.አ የሚጠናቀቅ ናቸውም ተብሏል።
በስምምነት ሥነ ሥረዓቱ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ከዚህ ቀደም በርካታ ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በመገንባት ለመማር ማስተማር ስራው ከፍተኛ አስተዋጻኦ ማበርከቱ ተገልጿል።
ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያመጡና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ተመርጠው የሚገቡባቸው ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ለመገንባት አቅዶ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
ትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የጥምህርት ጥራት እየቀነሰ መጥቷል በሚል የፈተና አሰጣጥ እና ሌሎች የጥራት ማስጠበቂያ መንገዶችን እየተከተለ ይገኛል፡፡
ልዩ ወይም አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከሌሎች መደበኛ ትምህርት ቤቶች ጋር ሲነጻጸሩ የተሸለ ጥራት ያላቸውን ተማሪዎች በማፍራ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
ለአብነትም በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም አዳሪ ትምህርት ቤቶች ብሔራዊ ፈተና ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ማሳለፍ ሲችሉ በሌሎች መደበኛ ትምህርት ቤቶች ከተፈተኑ ተማሪዎች መካከል የማለፊያ ውጤት ያመጡት ከ5 በመቶ በታች ናቸው፡፡