ኢትዮጵያ እስካሁን በሯን ለውጭ ባንኮች ዝግ አድርጋ የቆየች ሲሆን አሁን ላይ የፖሊሲ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የውጭ ሀገራት ባንኮች እንዲገቡ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል፡፡
ለዚህም ሲባል የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከአንድ ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን ዋና መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው ስታንዳርድ ባንክ በኢትዮጵያ ለመግባት ከስድስት ወራት በፊት አመልክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የሞሮኮ፣ የኬንያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባንኮች በኢትዮጵያ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋ፡፡
ዋና ገዢው አክለውም የውጭ ሀገራት ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሰሩ የሚፈቅደው ህግ በቀጣዮቹ ሳምንታት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚጸድቅ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንክ ፍቃድ ለማግኘት የሚፈልጉ ተቋማት ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል ለዉጪ ባንኮች 100 ሚሊዮን ብር እና ባንክ ላልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት 25 ሚሊዮን ብር ሀብት ሊኖራቸው ይገባል።
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች አምስት የሚደርሱ የባንክ ፈቃድ ለመስጠት ማቀዷን ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም የውጭ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፉም ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በጋራ የሚሰሩበት አማራጭ ሊኖር እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በባንክ፣ በቴሌኮም፣ በትራንስፖርት እና አቪዬሽን ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩ ቆይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ ተደርገው የቆዩ ዘርፎች ክፍት እንደሚደረጉ ቃል የገቡ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የውጭ ቴሌኮም የሆነው ሳፋሪኮም ከሶስት ዓመት በፊት ፈቃድ ማግኘቱም ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም የመንግሥት የልማት ድርጅት እና ብቸኛ የቴሌኮም ድርጅት ሆኖ የቆየውን የኢትዮ ቴሌኮም 45 በመቶ ድርሻ ለውጭ ባለሀብት በመሸጥ ሦስተኛ የውጭ ቴሌኮም ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ቢወጣም ተወዳዳሪ በመጥፋቱ ጨረታው ቀርቷል፡፡