የጣና ፎረም ጉባኤ ለሶስተኛ ጊዜ ተራዘመ

በባህር ዳር ከተማ ሊካሄድ የነበረው 11ኛው የጣና ፎረም ለሶስተኛ ጊዜ ተራዝሟል፡፡

የአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው እና በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ የሚካሄደው ዓመታዊው የጣና ፎረም ጉባኤ ለሶስተኛ ጊዜ ተራዘመ።

11ኛው ጉባኤ መጀመሪያ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው ባለፈው ዓመት ከጥቅምት 2-4 ቀን 2016 ዓ.ም ነበር።

ሆኖም ጉባኤው “ባልተጠበቁ ሁኔታዎች ምክንያት” እንደተራዘመ የፎረሙ ጽህፈት ቤት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደህንነት ጥናቶች ተቋም አስታውቆ ነበር።

ጉባኤው ሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ጽህፈት ቤቱ በጊዜው አስታውቆ የነበረ ቢሆንም በተባለው ጊዜ ሳይካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ተራዝሟል።

“አፍሪካ እየተሻሸለ በመጣው የዓለም ሥርዓት ውስጥ” የሚል መሪ ቃል የያዘው 11ኛው ጉባኤ ከጥቅምት 15-17 2017 ይካሄዳል ተብሎ ተጠብቆ ነበር

ነገር ግን ፎረሙ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ “11ኛው የጣና ከፍተኛ የጸጥታ ጉዳዮች ፎረም [እ.ኢ.አ] ወደ 2025 መተላለፉን የጣና ፎረም ሴክሬታሪያት ለማሳወቅ ይወዳል” ብሏል

ፎረሙ አክሎም የጣና ፎረም ሴክሬታሪያት ከጣና ፎረም ቦርድ ጋር በመሆን ፎረሙ የሚካሄድበትን ቀጣይ ቀን ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል

የጣና ፎረም የሚካሄድበት የአማራ ክልል ላለፈው አንድ ዓመት በፌደራል መንግስቱ እና በፋኖ ኃይሎች መካከል ውጊያ እየተካሄደበት ይገኛል፡፡

የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት የተጀመረው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ ግዕት እየተባባሰ መሄዱን ተከትሎ በክልሉ ለ10 ወራት የቆየ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የነበረ ሲሆን ካሳለፍነው ግንቦት ወር ጀምሮ ይህ አዋጅ ጊዜው ቢያበቃም ክልሉ ወደ ቀድሞ ሲቪል አስተዳድር አልተመለሰም፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እንዳስታወቀው በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እንዳልቻሉ አስታውቋል፡፡

ከሰኔ ወር ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ጦርነት ከ160 በላይ ዜጎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል፡፡

ግድያ ከተፈጸመባቸው ዜጎች መካከል የአዕምሮ ህመምተኞች፣ አዛውንቶች፣ ህጻናት እና ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *