195 ሀገራት በተሳተፉበት የሮቦቲክስ ውድድር ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች አሸናፊ ሆነዋል፡፡
ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ እድሜያቸዉ ከ14 እስከ 18 የሆኑ 5 ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች ከመስከረም 14 እስከ 20 በግሪክ በተከሄደው ዓለም አቀፉ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ከ195 በላይ ሀገራት በሚያሳትፈዉ የሮቦቲክስ ዉድድር ኢትዮጵያን ወክለዉ ችግሮችን እንዴት መፍታት ይችላሉ የሚለው ላይ ትኩረት አድርገው በውድድር ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ተወዳዳሪዎቹ በ2024 የፈርስት ግሎባል የሮቦቲክስ ቻሌንጅ ተማሪዎች በሮቦቲክስ በኩል በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ ፣ በምህንድስና እና በሂሳብ መስኮች ማበረታት ዓላማ ባደረገው የወደ ፊቱን መመገብ የሚል መርህ ያለው ውድድር ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ይህ ጭብጥ የሚያተኩረው የአለም የምግብ ዋስትናን እና ዘላቂ የግብርና አሰራሮችን መፍታት ላይ መሆኑንም ተወዳዳሪዎቹ ተናግረዋል።
ኢትዮጲያን የወከሉት ተወዳዳሪዎች ካሌብ ኤርሚያስ፣ ሚኪያስ ቴዎድሮስ ፣ ጺዮን ፍጹም፣ አቢጊያ ፍጹም ፣ እና ሰሎሜ ብርሃኑ ከአሰልጣኞቻቸው ዳግማዊ ግሩም እና ኖህ ጌታቸው ጋር በውድድሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ውድድሩን በሁለተኛ ደረጃነት አጠናቀው በድል ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አሰልጣኝ ዳግማዊ ግሩም ተናግሯል።
ውድድሩ 12 ዙሮች የነበሩት ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎቹ 8 የሚሆኑትን በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረስ ችለዋል፡፡
በፍጻሜ ላይ ከነበሩት ስድስት ዙሮች ደግሞ አራት የሚሆኑትን በማሸፍ በሁለተኛ ደረጃ ውድድሩን ማጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡
ውድድሩ ላይ ከአንድ እስከ ሶስተኛ የሚወጡት አራት አራት ሀገራት ሲሆኑ አንደኛ ደረጃ ያጠናቀቁት ቻይና ፣ማዳጋስካር ፣ ሞልዶቫ፣ ኩክ አይስላንድ ናቸው።
ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቁት ኢትዮጵያ ፣ ኡዝቤኪስታን ፣ ካምቦዲያ እና ፖላንድ ሲሆኑ እንዲሁም በሶስተኛ ደረጃ አሸናፊ የሆኑት ሲንጋፖር ፣ኢስዋትኒ፣ ጓቲማላ ፣ትሬንዳድና ቶቤጎ የመጡ ተወዳዳሪዎች መሆናቸውን ተነግሯል፡፡
ተወዳዳሪዎቹ በአፍሪካ ላይ ያለውን የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የሂሳብ የትምህርት ክፍሎች ድክመት መኖሩን ገልጸው ለዚህ መፍትሄ ለመሆን እንደሚሰሩ አንስተዋል፡፡
በግሪክ የተካሄደው ውድድሩ ስፖርታዊ ይዘት የነበረው ሲሆን የሮቦቲክስ ዉድድሩን ፈርስት ግሎባል እና ሬድ ሮቦቲክስ በየዓመቱ አንድ ላይ በመቀናጀት እንደሚያዘጋጁት አሰልጣኝ ዳግማዊ ግሩም ገልጿል ።
ተማሪዎች ከምግብ ምርት፣ ስርጭት እና ዘላቂነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ሮቦቶችን በመንደፍ እና በማዘጋጀት በውድድሩ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።
የምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል፣ ብክነትን ለመቀነስ እና የግብርና ቅልጥፍናን ለመጨመር የሚረዱ አዳዲስ መፍትሄዎችን እንዲያዘጋጁ ተበረታትተዋል።
አምስቱ ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች ከ2017 ጀምሮ የተለያዩ ዉድድሮች ላይ ሲሳተፉ የነበረ ሲሆን የአሁኑን ውድድራቸውን ያደረጉት በግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዉድድሩ የተለያዩ ክህሎቶችን ለማዳበር ከሚሰጠዉ ጥቅም ባሻገር ታዳጊዎቹ ከራሳቸዉ አልፎ በሀገር እንዲሁም በአለም ላይ የተከሰተን ዉስብስብ ችግር መፍታት እንዲችሉ እንደሚያግዛቸውም ተወዳዳሪዎቹ ተናግረዋል፡፡