የተትረፈረፈ የነዳጅ ሀብት ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ደቡብ ሱዳን ከዚህ በፊት ነዳጇን በሱዳን በኩል አድርጋ ለዓለም ገበያ ስታቀርብ ቆይታለች፡፡
ሱዳን በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መሆኗን ተከትሎ እስከ ፖርት ሱዳን የተዘረጋው የደቡብ ሱዳን ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር በጦርነቱ ወድሞባታል፡፡
በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ በኢትዮጵያ በኩል እስከ ጅቡቲ ወደብ ድረስ የተዘረጋ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ማቀዷ ተገልጿል፡፡
በቻይና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሲሳተፉ የነበሩት ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በኢትዮጵያ በኩል እስከ ጅቡቲ ወደብ ድረስ የሚዘረጋ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ዙሪያ መክረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከቻይና ብሔራዊ ነዳጅ ኮርፖሬሽን ሃላፊ ዳይ ሁሊያንግ ጋር በቤጂንግ መምከራቸውን የደቡብ ሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ የቻይናው ነዳጅ ኮርፖሬሽን ከደቡብ ሱዳን ተነስቶ በኢትዮጵያ በኩል አድርጎ ጅቡቲ ወደብ ድረስ የተዘረጋ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ፈቃደኛ የሆነ ሲሆን በግንባታ ወቅት ለሰራተኞች ደህንነት ጥበቃ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
ስምመነቱ ከነዳጅ ማስተላለፊያ ግንባታ ባለፈም አዲስ የነዳጅ ጉድጓድ ፍለጋንም እንደሚያካትት በዘገባው ለይ ተጠቅሷል፡፡
ደቡብ ሱዳን 90 በመቶ ኢኮኖሚዋ በነዳጅ ሽያጭ ለይ የተመሰረተ ሲሆን የሱዳን እርስ በርስ ጦርነት በዚህ ገቢዋ ላይ ከፍተኛ የተባለ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ከአምስት ወራት በፊት በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የሚዋስን 220 ኪሎ ሜትር መንገድ ገነባል የተባለ ሲሆን የግንባታ ወጪውን ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን 738 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ተስማምታለች፡፡