የኢትዮጵያ አየር ሀይል ከሶማሊያ ጋር የምትዋሰንበት ምስራቁን የአየር ክልል በንቃት እየጠበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል
ከሰሞኑ ግብፅ እና ሶማልያ በቀጠናው እያረጉት ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር ሀይል የምስራቁን የአየር ክልል በንቃት እየጠበቀ እንደሚገኝ ገልጿል።
በኢትዮጵያ አየር ሃይል የ3ኛው አየር ምድብ የተሰጠውን ሃገራዊ ግዳጅና ተልዕኮ ለመወጣት በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የአየር ምድቡ አዛዥ ኮሎኔል ደረጀ ቡሽሬ ገልፀዋል፡፡
አዛዡ የ3ኛው አየር ምድብ የሃገራችንን ብሎም የምስራቁን የአየር ክልል በንቃት እየጠበቀ የሚገኝ የሃገር መከታና መመኪያ የሆነ ምድብ ነው ያሉ ሲሆን “ወደፊትም ኢትዮጵያን ከውስጥም ይሁን ከውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ለመጠበቅ በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል” ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር የምስራቅ ዕዝ በተሟላ ወታደራዊ ዝግጁነት ላይ ይገኛል ብሏል።
“በተለያዩ ዘመናት ሀገራችንን ለመውረርና የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የሚሞክሩ ሀይሎችን በመከላከል በመስዋዕትነት የተረከቡትን አደራ ለማስቀጠል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል በተሟላ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ” ሲል መከላከያ አሳውቋል።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ከዘጠኝ ወር በፊት በአዲስ አበባ የወደብ መግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ስምምነትን ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው የተበላሸ ሲሆን ሶማሊያ ከግብጽ እና ቱርክ ጋር ወታደራዊ ስምምነቶችን አድርጋለች፡፡
ግብጽ ወታደሮቿን እና የጦር መሳሪያ ወደ ሶማሊያ በማጓጓዝ ላይ ስትሆን በቀጣዮቹ ሳምንታትም ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ማቀዳቸው ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊላድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ በአፍሪካ ቀንድ አዲ ውጥረት የተፈጠረ ሲሆን ምዕራባዊን ሀገራት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሶማሊያ እንቅስቃሴ የአፍሪካ ቀንድን ወዳልተፈለገ ትርምስ የሚያስገባ ነው በሚል ከድርጊቷ እንድትታቀብ በተለያዩ ጊዜያት አሳስባለች፡፡
ቱርክ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ለማስማማት በአንካራ እያደራደረች ሲሆን ሀምሌ እና ሰኔ ወር ላይ የተካሄዱ ድርድሮች ያለስምምነት መጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ሌላኛዋ ጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ሶማሊያን እና ኢትዮጵያን ለማስማማት ታጁራ የተሰኘውን ወደብ ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን ከጅቡቲ የቀረበላትን የወደብ ስጦታ ስለመቀበሏ ወይም አለመቀበሏ በይፋ ያለችው የለም፡፡
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀስላሴ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ በሶማሊያ መወረሯን እንደማትረሳ ተናግረዋል፡፡