በደቡብ አሜሪካዋ ፔሩ ሊማ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድር ትናንት ጠናቋል፡፡
በዚህ የአትሌቲክ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከአሜሪካ በመቀጠል ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች፡፡
ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፈው ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በ6 ወርቅ፣ 2 ብር እና 2 ነሐስ በአጠቃላይ 10 ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ ችሏል።
በዚህ ኢትዮጵያ ከዓለም አሜሪካን በመከተል 2ኛ እንዲሁም ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ያጠናቀቀች ሲሆን፤ ውድድሩን 1ኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀች አሜሪካ በ8 ወርቅ፣ 4 ብር እና 4 ነሃስ በድምሩ 16 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች
በአትሌት መዲና ኢሳ በ5000 ሜትር፣
በአትሌት ሲምቦ አለማየሁ በ3000 ሜትር መሰናክል
በአትሌት ጀነራል ብርሃኑ በ800 ሜትር፣
በአትሌት አለሺኝ ባወቀ በ3000 ሜትር ሴቶች
በአትሌት ሳሮን በርሀ በ1500 ሜትር እና
በአትሌት አብዲሳ ፈይሳ በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል።
በተጨማሪም አትሌት መቅደስ ዓለምእሸት እና አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በተመሳሳይ ርቀት በ5000 ሜትር የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል ።
አትሌት ማርታ አለማየሁ በ3000 ሜትር ሴቶችና አትሌት ኃይሉ አያሌው በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግበዋል ።
በዚህ ሻምፒዮና በ800 ሜትር፣ በ1500 ሜትር፣ በ3000 ሜትር፣ በ5000 ሜትር፣ በ3000 ሜትር መሠናክል በሁለቱም ፆታ እንዲሁም በ10000 ሜትር ሴቶች እርምጃ 11 ሴት፣ 8 ወንድ በአጠቃላይ 19 አትሌቶች ኢትዮጵያን ወክለው መሳተፋውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያለክታል።
በፔሩ ሊማ በተካሄደው የአለም ከ20 አመት በታች የአትሌቲክ ሻምፒዮና 134 ሀገራትን የተሳተፋበት ሲሆን፤ 34 ሃገራት በሜዳልያ ሰንጠረዥ መግባት ችለዋል።
በሌላ ዜና ኢትዮጵያ በፓሪስ ፓራሊምፒክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ አሸንፋለች።
አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ለኢትዮጵያ በ2024ቱ የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች።
ለ17ኛ ጊዜ በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው የፓራሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ በ 1,500 ሜትር ጭላንጭል ውድድር በአትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ አማካኝነት ማግኘት ችላለች።
አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በፓራሊምፒክ ውድድር ታሪክ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ያመጣች ሲሆን ከአራት አመታት በፊት በቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር በተመሳሳይ ርቀት ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመሪያ የፓራሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘት ችላለች።