በየ አራት አመቱ አንዴ የሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር በፓሪስ ሲካሄድ 15ኛ ቀኑን ይዟል።
206 ሀገራት በሚሳተፉበት በዘንድሮው ውድድር ከ10 ሺህ 500 በላይ አትሌቶችም እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡
ዛሬ ረፋድ በተካሄደው የወንዶች ማራቶን ውድድር አትሌት ታምራት ቶላ ርቀቱን በ2:06:26 በሆነ ሰዓት አሸንፏል፡፡
አትሌት ታምራት ቶላ ውድድሩን የጨረሰበት ሰዓት አዲስ የኦሎምፒክ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ እንዳሸነፈም ተገልጿል፡፡
ውድድሩን ቤልጂየማዊው በሽር አብዲ ሁለተኛ እንዲሁም ኬንያዊው ቤንሰን ኪፕሩቶ ደግሞ ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡
አትሌት ታምራት ቶላ ከውድድሩ በኋላ እንዳለው “ውድድሩን በማሸነፌ እና የወርቅ ሜዳልያውን ለሀገሬ ኢትዮጵያ በማስገኘቴ በጣም በጣም ተደስቻለሁ” ሲል በእምባ ታጅቦ አስተያየቱን ሰጥቷል።
አትሌት ታምራት ቶላ በውድድሩ በ2:06:26 በሆነ ሰዓት በመግባት በወንዶች ማራቶን የኦሎምፒክ ሪከርድ ባለቤት መሆን ችሏል።
በሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን 39ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ አትሌት ደሬሳ ገለታም 5ተኛ ደረጃ በመውጣት ውድድሩን አጠናቋል፡፡
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ ወንዶች ማራቶን ውድድር በጣም ከባድ እንደነበር ከውድድሩ በኋላ ተናግሯል።
የፓሪስ ኦሎምፒክ ውድድር ቦታ “በጣም አስቸጋሪ ነበር“ ሲል የገለፀው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ “እግሮቼን የሆነ ስሜት ተሰምቶኛል“ ሲል ከውድድሩ በኋላ አስተያየቱን ሰጥቷል።
የ 42 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በኦሎምፒክ ማራቶን የመወዳደር እድሉ ትንሽ እንደዘገየ እና ምናልባት በሪዮ ወይም ቶኪዮ ኦሎምፒክ ቢሆን ሜዳሊያ ሊያገኝ እንደሚችል ገልጿል።
በማራቶን ውድድር የተገኘው የፓሪስ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ ሲሆን ኢትዮጵያ ደረጃዋን ከ68ኛ ወደ 44ኛ አሻሽላለች፡፡
አትሌት ታምራት በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኦሪጎን የማራቶን አሸናፊ የነበረ ሲሆን በኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በፓሪስ አግኝቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አትሌቱ በኦሎምፒክ ውድድሮች ሜዳሊያ ሲያገኝ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በ2016 በተካሄደው የሪዮ ኦሎምፒክ ላይ በ10 ሺህ ሜትር ተወዳድሮ ሶተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ነበር።
አትሌት ታምራት ቶሎ በፓሪስ ኦሎምፒክ ተጠባባቂ የነበረ ሲሆን አትሌት ሲሳይ ለማ መጎዳቱን ተከትሎ በውድድሩ እንዲሳተፍ መደረጉ ይታወሳል።
አትሌት ገዛኸኝ አበራ ከ24 ዓመት በፊት በ1982 ዓ.ም በአውስትራሊያ ሲድኒ ኦሎምፒክ ላይ ለኢትዮጵያ በማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ካስገኘ በኋላ ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈ አትሌት አልነበረም፡፡
ኢትዮጵያ በሲድኒው ኦሎምፒክ በአትሌት ሀይሉ ገብረስላሴ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ደራርቱ ቱሉ እና ገዛሐኝ አበራ አማካኝነት አራት ወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታ ነበር፡፡
አበበ ቢቂላ ሁለት ጊዜ፣ ማሞ ወልዴ ገዛኸኝ አበራ እና ታምራተ ቶላ በኦሎምፒክ የወንዶች ማራቶን ውድድር ታሪክ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያመጡ አትሌቶች ናቸው፡፡