ብሔራዊ ባንክ በልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ አንድ ዶላርን በ107 ነጥብ 9 ብር ሸጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ  ባንክ ለባንኮች ዶላር ለመሸጥ ያወጣው ልዩ ጨረታ ውጤትን ይፋ አድርጓል።

በዛሬው እለት በተካሄደው ልዩ ጨረታ 27 ባንኮች የሚፈልጉትን የዶላር መጠን እና የሚገዙበትን ዋጋ አስገብተው ተጫርተዋል።

ባንኮቹ ለአንድ የአሜሪካ ዶላር ያቀረቡት አማካይ የመግዣ ዋጋ 107.9 ብር መሆኑን ባንኩ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።

ጨረታው በነገው እለት ባንኮች በሚያወጡት እለታዊ የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ እንዲመጣ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ብሏል ብሔራዊ  ባንክ።

የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ የዶላር ሽያጭ ጨረታው ውጤትን ሲገልጹ ባለፉት ቀናት በባንኮች እና በብላክ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የውጭ ምንዛሬ መረጋጋትን ያመጣል ያሉት አቶ ማሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁሉንም የውጭ ምንዛሬ እንቅስቃሴ ወደ ባንክ ስርአት የማስገባት እቅድ መያዙን አብራርተዋል።

በዚህም የውጭ ምንዛሬ የሚሹ አስመጪዎችና ሌሎች ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም ይገጥማቸው የነበረው ችግር እንደሚፈታ ዋና ገዢው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲመራ ካደረገች በኋላ ባንኮች አስመጪ ደንበኞቻቸው ለሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ እየሰጡት ያለው ምላሽ አበረታች መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄደችው ልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ማዕከላዊ ባንኮች ከንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የሚገዙበት ወይም የሚሸጡበት አሰራር ነው።

ጨረታው በውጭ ምንዛሬ ገበያው ላይ የሚታይ ጫናን ለማቃለልና በግልና መንግስት መካካል ያለውን የምንዛሬ ልዩነት ለማጥበብ እንደሚረዳ ይታመናል።

ብሔራዊ ባንክ በገበያ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ በቀጣይ ሳምንታትም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ በጨረታ ሊሸጥ እንደሚችል አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ተግባራዊ ካደረገች ዛሬ 10ኛ ቀኗን የያዘች ሲሆን የዶላር የምንዛሬ ዋጋ ከ40 ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

አሁን ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በባንኮች 100 ብር እና ከዛ በላይ እየተገዛ ሲሆን ሽያጩ ደግሞ ከ110-115 ብር እየተከናወነ ይገኛል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *