ጸረ ሙስና ኮሚሽን የ113 አመራሮችን ሃብት እያጣራ መሆኑን አስታወቀ

የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በ2016 በጀት አመት ሃብታቸውን ካስመዘገቡት አመራሮች መካከል በተጨማሪም የሃብት ማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በአንድ መቶ አስራ ሦስት ውሳኔ ሰጪ አመራሮች ላይ የሃብት ማጣራት ስራ እየሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ የሙስና መረጃ አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን በላይነህ ተናረዋል፡፡

ያስመዘገቡት ሃብት አጠራጣሪ ሁኖ በተገኙና በተደረጉ ጥቆማዎች መሰረት በውሳኔ ሰጪ አመራሮች ላይ የሃብት ማጣራት ሥራ እየተሰራ እንዳለ ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሚሰራው የሃብት ማጣራት ሥራ ሃታቸው ለሙስና የተጋለጡትን ለፍትህ ሚኒስቴር እንደሚሳውቅም ጠቁመዋል፡፡

ሃብታቸው እየተጣራ ያሉትን ውሳኔ ሰጪ አመራሮች በአሁኑ ሰዓት ይፋ ማድርጉ ያልተመዘገቡ ሃብቶችን እንዲያሸሹ ስለሚያደርግ ከማጣራት ሥራው በኋላ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ከህብረተሰቡ ጋር በይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ሙስናና ብልሹ አሰራርን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሥራ አስፈፃሚው አጽንኦት አድርገውበታል፡፡

የፌደራል የስነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት የመንግስት አመራሮች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ስራን መስራት እንዳይችሉ የሚደነግግ ረቂቅ ደንብ እያዘጋጀ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

እንዳስታወቀው ማንኛውም የመንግስት አመራር ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ንግድ እና መስል ስራዎችን መስራት የሚከለክል ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የመንግስት አመራሮች ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተለዩ ዘርፎች ውስጥ መሆናቸው የሚናገሩት የኮሚሽኑ የሙስና መረጃ አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን በላይነህ በህዝብ ሃብት ላይ ውሳኔን የሚያሳልፉ አካላት የመንግስትና የህዝብን ስራ ብቻ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ለከፍተኛ ባለስልጣናት የጥቅም ግጭት መከላከል እና የሥነ-ምግባር ደንብ ረቂቅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን የሚናገሩት ሥራ አስፈፃሚው፤ አመራሮች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎችን ሲሰሩ የጥቅም ግጭቶች እንደሚከሰቱ እና አግባብ ባልሆነ መንገድ የህዝብና የመንግስት ሃብትንም ሊመዘብሩ ስለሚችሉ ያንን ለመከላከል ያለመ ረቂቅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡        

የረቂቅ ደንቡ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቶሎ ምልሽ ሊሰጥበት እንደሚገባ የተናገሩት ሥራ አስፈፃሚው ደንቡ ከፀደቀ ኮሚሽኑም ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ስራን እየሰሩ ባሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ምርመራ እንደሚጀምር አክለው ተናግረዋል።

ጸረ ሙስና ኮሚሽን የመንግሥት ባለስልጣናትን ሃብት እና ንብረት በመመዝገብ ላይ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የገለጸ ሲሆን ከወረዳ ጀምሮ እሰከ የፌደራል ክፍተኛ ባለስልጣናት የሚገኙ የ180 ሺህ ግለሰቦች በላይ ሃብትና ንብረት ተመዝግቧል ብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *