የመንግስት አመራሮች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ስራን መስራት እንዳይችሉ የሚደነግግ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጀ፡፡
የፌደራል የስነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዳስታወቀው ማንኛውም የመንግስት አመራር ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ንግድ እና መስል ስራዎችን መስራት የሚከለክል ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የመንግስት አመራሮች ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተለዩ ዘርፎች ውስጥ መሆናቸው የሚናገሩት የኮሚሽኑ የሙስና መረጃ አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን በላይነህ በህዝብ ሃብት ላይ ውሳኔን የሚያሳልፉ አካላት የመንግስትና የህዝብን ስራ ብቻ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለከፍተኛ ባለስልጣናት የጥቅም ግጭት መከላከል እና የሥነ-ምግባር ደንብ ረቂቅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን የሚናገሩት ሥራ አስፈፃሚው፤ አመራሮች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎችን ሲሰሩ የጥቅም ግጭቶች እንደሚከሰቱ እና አግባብ ባልሆነ መንገድ የህዝብና የመንግስት ሃብትንም ሊመዘብሩ ስለሚችሉ ያንን ለመከላከል ያለመ ረቂቅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የረቂቅ ደንቡ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቶሎ ምልሽ ሊሰጥበት እንደሚገባ የተናገሩት ሥራ አስፈፃሚው ደንቡ ከፀደቀ ኮሚሽኑም ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ስራን እየሰሩ ባሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ምርመራ እንደሚጀምር አክለው ተናግረዋል።
ጸረ ሙስና ኮሚሽን የመንግሥት ባለስልጣናትን ሃብት እና ንብረት በመመዝገብ ላይ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የገለጸ ሲሆን ከወረዳ ጀምሮ እሰከ የፌደራል ክፍተኛ ባለስልጣናት የሚገኙ የ180 ሺህ ግለሰቦች በላይ ሃብትና ንብረት ተመዝግቧል ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ ሌሎችም ባለስልጣናት ከዚህ በፊት ሀብታቸውን ቢያስመዘግቡም በየጊዜው እየታደሰ እንዳልሆነ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
አንድ የመንግሥት ሠራተኛም ሆነ ባለስልጣን ሀብቱን ካስመዘገበ በኋላ በየሁለት ዓመቱ ማሳደስ እንደሚጠበቅበት ቢታወቅም አመራሮች የእድሳት ዘመኑን ጠብቀው ሀብታቸውን እያሳደሱ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡
መቀመጫውን ጀርመን በርሊን ከተማ ያደረገው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ በየዓመቱ የሙስና ቅኝት ጥናት በማካሄድ የአገሮችን የሙስና ሁኔታ የሚያሳይ ደረጃና ውጤት ይፋ ያደርጋል፡፡
ድርጅቱ በ2023 የሀገራት የሙስና ተጋላጭነት ሪፖርቱ ላይ እንደገለጸው ኢትዮጵያ ከአገሮቹ መካከል በ37 ነጥብ 98ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
ነጥቡ የሚሰጠው ከ100 ሲሆን፣ 100 ያገኘ አገር የሙስና ተጋላጭነቱ ንፁህ የሚባል ሲሆን ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበ አገር ደግሞ አስከፊ የሙስና ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ መለኪያ መሠረት በ2023 በ37 ነጥብ 98ኛ ደረጃን፣ በ2022 38 ነጥብ በማግኘት 94ኛ፣ በ2021 በ39 ነጥብ በማግኘት 87ኛ፣ በ2020 በ38 ነጥብ በማስመዝገብ 94ኛ ተቀምጣ ነበር፡፡