ኢትዮጵያ በየዓመቱ 100 ሺህ ሔክታር መሬት በአዲስ የቡና ዝርያ እየተካች መሆኗ ተገለጸ

የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ላይ ባደረሱት ጥቃት የኢትዮጵያ ቡና ንግድ ለሶስት ቀናት ተስተጓጉሎ እንደነበር ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በ2016 በጀት ዓመት የውጪ ንግድ አፈጻጸም ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ውስጥ 350 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር ብለዋል፡፡

ይሁንና አፈጻጸሙ 298 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ሀገራት የምትልከው ቡና በቀይ ባህር በኩል በመሆኑ እና የሀውቲ ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃት ምክንያት መስጓጎል ገጥሞት እንደነበርም ተገልጿል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ኤምሲ መርከብ በኩል ወደ አውሮፓ ሀገራት በመጓጓዝ ለይ እያለ በሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት ምክንያት የቡና ንግድ እስከ ሶት ቀናት ድረስ በመስተጓጎሉ ምክንያት ኢትዮጵያ ከቡና ንግድ ማግኘት የነበረባትን ገቢ እንዳታገኝ አድርጓል፡፡

የሀውቲ ታጣቂዎች በቀጣይ የቡና ንግድ ላይ ስጋት ሊደቅኑ እንደሚችሉ፣ ነጋዴዎች ምርቶች በወደቦች ላይ ሲቆዩ ለተጨማሪ ወጪ እንዲሁም ይህን ሽሽት ቡናን በአየር ትራንስፖርት ሲልኩ ላልተፈለገ ወጪ ሊዳርጋቸው እንደሚችልም አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት የቡና ምርቶቿን ወደ 65 የዓለማችን ሀገራት ልካለች የተባለ ሲሆን ከተላከው ጠቅላላ ቡና ውስጥ 21 በመቶው ወደ ሳውዲ አረቢያ እንደተላከ ተገልጿል፡፡

አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ቻይና፣ ጃፓን እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ከላከችባቸው ዓለማችን ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከቡና ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ህገወጥ የቡና ግብይትን መቆጣጠር፣ የምርት ጥራን ማሳደግ እና የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን እያለማች መሆኗን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ያረጁ ቡናዎች ካልተነሱና ካልተቀየሩ በስተቀር ምርትና ምርታማነት እንደማያድግ በመረዳት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ 100 ሺህ ሄክታር ላይ ያሉ የአረጁ ቡናዎችን የማንሳትና በአዲስ የመትከል ስራ እየተሰራ ነውም ተብሏል።

ከአራት ወራት በፊት የአውሮፓ ህብረት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚል የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ከሚያውኩ በተለይም የደን ውጤቶች የሆኑ ምርቶች ወደ ህብረቱ አባል ሀገራት እንዳይገቡ በሚል እገዳ መጣሉ ይታወሳል፡፡

ይህ የህብረቱ እገዳ ከሚመለከታቸው ሀገራት መካከል የኢትዮጵያ ቡና ምርት አንዱ ሲሆን ኢትዮጵያ ለቡና ምርት በሚል ጫካ እንደማትመነጥር አስታውቃለች፡፡

ይሁንና በኢትዮጵያ ለቡና ምርት በሚል የሚመነጠረው ደን መጠን  2 ሄክታር ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የደን ጭፍጨፋ የሌለበት የቡና ምርት ለዓለም አቀፉ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡

የአውሮፓ ህብረት በተመነጠረ ጫካ ውስጥ የተመረተ ቡና አልቀበልም ማለቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በቡና ምርቷ ላይ ማስተካከያ እያደረገች መሆኑ ተገልጿል።  

የኢትዮጵያ ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሆነው የቡና ምርት ወደ አውሮፓ ገበያ የሚገባ በመሆኑ ይህንን የገበያ እድል ላለማጣት ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ከቡናና ሻይ ባለስልጣኑ ያገኘው ምላሽ ያስረዳል።

ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ገበያ ከምታቀርበው የቡና ምርት በዓመት 500 ሚሊየን ዶላር እንደምታገኝ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ተናግረዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *