ባሳለፍነው ሳምንት ከደባርቅ ዩንቨርሲቲ ተነስተው ወደ ቤተሰቦቻቸው በመጓዝ ላይ የነበሩ ተማሪዎች መታገታቸው ይታወሳል፡፡
እገታው የተፈጸመው ለአዲስ አበባ ከተማ ትንሽ ሲቀራቸው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ በታጣቂዎች እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾም ነበር፡፡
የፌደራል መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግስት እስካሁን ስለ ጉዳዩ በይፋ እስካሁን ያሉት ነገር ባይኖርም የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ግን ልጆቻቸው በታጣቂዎች እንደታገቱባቸው ለተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ በጉዳዩ ዙሪያ በወጣው መግለጫ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተራዘሙ ግጭቶች የህግ የበላይነት እንዳይከበር ምክንያት ሆነዋል ሲል በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ላይ ገልጿል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት እና ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ተከታታይ እገታዎች ወንጀለኞችን እንዳይጠየቁ ማድረጉን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አረቪን ማሲንጋ መናገራቸውን ኢምባሲው አስታውቋል፡፡
አምባሳደር ማሲንጋ አክለውም ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ተማሪዎችን እና ንጹሀንን ማገት መቆም አለበት ያሉ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ከ100 በላይ ተማሪዎች እና ሌሎች መንገደኞች በታጣቂዎች እንደታገቱ ተናግረዋል ተብሏል፡፡
አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ምዕራባዊን ሀገራት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ በተደጋጋሚ ባወጧቸው መግለጫዎች መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት በክልሎቹ ካሉ ታጣቂዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ እንደሆነ በተደጋጋሚ የገለጸ ሲሆን በተለይም ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወይም ኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ የተደረጉ ድርድሮች ያለ ስምምነት መጠናቃቸው አይዘነጋም፡፡
የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት የተጀመረው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ ግዕት እየተባባሰ መሄዱን ተከትሎ በክልሉ ለ10 ወራት የቆየ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የነበረ ሲሆን ካሳለፍነው ግንቦት ወር ጀምሮ ይህ አዋጅ ጊዜው ቢያበቃም ክልሉ ወደ ቀድሞ ሲቪል አስተዳድር አልተመለሰም፡፡