ለኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር አዲስ ሀላፊ ተሾመለት

ዳንኤል ኃ/ሚካኤል የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ዋና ስራ አስፈፃሚ ተደርገው ተሾመዋል፡፡

የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር (ኢዲአር) ቺፍ ቴክኒካል ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ኢንጂነር ዳንኤል ኃ/ሚካኤል ከሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነዉ ተሾመዋል።

የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ለኢትዮ ጂቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ በነበሩት አብዲ ዘነበ ምትክ ዳንኤልን ኃ/ሚካኤልን ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈፃሚ እንዲሆኑ መድበዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተጓዦችና የጭነት አገልግሎት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱ ይታወሳል።

ማኅበሩ በየቀኑ ከ700 እስከ 1 ሺህ ሰዎችን የማጓጓዝ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ155 ሺህ በላይ ተጓዦችን እና 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን የጭነት አገልግሎት በማጓጓዝ የዕቅዱን 98 በመቶ አሳክቻለሁ ብሎ ነበር፡፡

ከ13 እስከ 15 በመቶ የየሀገሪቱን ወጪ እና ገቢ ምርት የሚያጓጉዘው ይህ የባቡር መስመር ከፈረንጆቹ 2024 ጥር ወር ጀምሮ ኢትዮጵያ የማስተዳደር ኃላፊነት ወስዳ እየሰራች ትገኛለች፡፡

በባቡር ትራንስፖርት ምቹ ምኅዳር በመፍጠርም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የገቢና ወጪ ምርት የማጓጓዝ አቅም የበለጠ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ከ1 ሺህ በላይ የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮች የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ምርት በማጓጓዝ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት እየደገፉ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት የሁለቱን ሀገራት ዜጎች በማገናኘት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ውስጥ ሶስት ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቶ ነበር።

752 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ከፈረንጆቹ ጥር 2018 ጀምሮ የመንገደኞች እና የእቃ ማጓጓዝ ትራንስፖርት በመስጠት ላይ ይገኛል።

የባቡር መስመር ፕሮጀክቱ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ 70 በመቶው ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር 30 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ ተገንብቷል።

የዓለም ባንክ ለኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር 730 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ታወሳል፡፡

የ730 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነቱን ገንዘብ ሚኒስቴርና የዓለም ባንክ ለአፍሪካ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክት (በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር ፕሮጀክት) ባሳለፍነው ነሀሴ ተፈራርመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን 90 በመቶ የባህር ንግድን የሚይዘው ስትራቴጂካዊው ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ ኮሪደር ጋር በተሳሰረ መልኩ የኢትዮጵያን የሎጅስቲክስና የትስስር አቅም እንደሚያጎለብት ተጠቁሟል።

በስምምነቱ መሰረት ለሜኦሶ -ድሬዳዋ መንገድ ግንባታ የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፤ ግንባታው የትራንስፖርት አቅምና ብቃት የሚጨምር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *