ኩዌት ኢትዮጵያዊን ሰራተኞችን ለመቅጠር ተስማማች

ኢትዮጵያና ኩዌት የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ኢትዮጵያና ኩዌት በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እና በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ናይፍ ሃኘስ አል ኦይታይቢ ፈርመውታል።

በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሠለሞን ሶካ እና ዳንኤል ተሬሳ፣ በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሰኢድ ሙሁመድ፣ በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ናይፍ ሃኘስ አል ኦይታይቢን ጨምሮ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ስምምነቱ ወደ ኩዌት የሥራ ስምሪት የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን መብትና ጥቅማቸው ተጠብቆ ህጋዊ የስራ ዕድል የሚያገኙበትን የትብብር ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገልጿል።

በነዳጅ የበለጸገችው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር ኩዌት የሦስት ወራት አስገዳጅ ስልጠና የወስዱ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን ለመቀበል ከዚህ በፊት ከመንግሥት ጋር ለመፈራረም እንደምትፈልግ ገልጻነበር።

ከስምምነቱ በኋላ በኢትዮጵያ የሚገኙ 600 የሚሆኑ የሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሰው ኃይል በማቅረብ ይሰራሉም ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያን ሰራተኞች ወደ ኩዌት ለስራ ለመጓዝ ቢያንስ ብቃቱ ከተረጋገጠ ተቋም የ3 ወር ስልጠና መውሰድ በግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

ኩዌት ከዚህ በፊት የቤት ሰራተኞች የምታገኘው ከፊሊፒንስ ሲሆን፤ በኹለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ አገሪቱ የሰራተኛ እጥረት በማጋጠሙ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን ለመቀበል ማቀዷ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከኩዌት መንግሥት ጋር በተስማሙት መሰረት፤ አንድ ሰራተኛ በወር 90 ኩዌት ዲናር ወይም 300 ዶላር ይከፈለዋል የተባለ ሲሆን፤ ይህም በወቅታዊው የምንዛሬ ተመን ወደ 18 ሺሕ የኢትዮጵያ ብር ይጠጋል፡፡

ወደ ፊትም ወርሃዊ ክፍያዉ እስከ 500 ዶላር ከፍ ሊል እንደሚችልም የተገለጸ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ኩዌትን ጨምሮ ከቤሩት፣ ከእስያ እና አውሮፓ አገራ ጋር የስምምነት ሥራዎች እንደተጀመሩ መግለጹ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ሰራተኞችን በማቅረብ ጥሩ ልምድ ያላት ሲሆን በሳውዲ አረቢያ ብቻ በዚሕ አመት 500 ሺህ ዜጎችን ለመላክ ማቀዷን ከወራት በፊት ተናግራለች፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው እና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እስር ቤት ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይም ትገኛለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ በሌሎች የአረብ ሀገራት እስር ቤቶች ያሉ 70 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ለመመለስ እቅድ መያዙን አስታውቋል፡፡

ካሳለፍነው ሚያዝያ ወር ጀምሮም 30 ሺህ ኢትዮጵያዊያን በሳውዲ አረቢያ መነግስት፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት እና ሌሎች ተባባሪ ተቋማት አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *