የሀገር መከላከያ ሰራዊት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ እንዳለው “የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ማሪን ኮማንዶ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ተሰማርቷል” ብሏል።
ተቋሙ የባህር ሀይል ዋና አዛዥ ተወካይ ሬር አድሚራል ናስር አባዲጋን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው “ጽንፈኛ” ባላቸው ቡድን አባላት ላይ እርምጃ እንደወሰደ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ማሪን ኮማንዶዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ባሉ ወረዳዎች እንደተሰማሩ እና ግዳጃቸውን እየተወጡ እንደሆነም አዛዡ መናገራቸው ተገልጿል።
እንዲሁም ማሪን ኮማንዶ በመርከብ ላይ በባህር ከሚሰጠው ተልዕኮ በተጨማሪ በማንኛውም ጊዜ ግዳጁን የሚወጣ ሀይል እንደሆነም ሬር አድሚራል ናስር አባድጋ ተናግረዋል ተብሏል።
ማሪን ኮማንዶ ከአማራ ክልል የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን በወሰዳቸው እርምጃዎች የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱንም በዚሁ ዘገባ ላይ ተጠቅሷል።
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን “መልሼ አደራጃለሁ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የ”ፋኖ” ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል።
የፍትህ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቲየስ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት በአማራ ክልል በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው ውጊያ ንጹሀን ዜጎች ከጥቃት እየተጠበቁ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ተመድን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርት ላይ ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በባህር ዳር፣ መራዊ፣ ማጀቴ እና ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት ንጹሀንን ሆን ብለው እንደገደሉ ተቋማቱ በሪፖርቶቻቸው ላይ የተገለጸ ሲሆን የፌደራል መንግሥት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን ውድቅ አድርጓል።
ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ የባህር ሃይሏን ለማዘመን የፈረንሳይን ድጋፍ እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡
በዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ያለችዉ ኢትዮጵያ ለባህር ሃይል ልማት ፊቷን ወደ ፈረንሳይ ማዞሯ ተገልጿል፡፡
በቀይ ባህር አከባቢ ያለዉ ዉጥረት ኢትዮጵያ ለአጠቃላይ ደህንነት በስፍራዉ የባህር ሃይሏን ለማሰማራት እንድታስብ እንዳደረጋት አስታውቃለች።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ ከፈረንሳይ ብሔራዊ መከላከያ እና የጦር ኃይሎች ብሔራዊ ምክር ቤት ኮሚቴ ተወካዮች እና ከቋሚ ኮሚቴዉ አባላት ጋር ተወያይተዋል።
በስብሰባዉ ላይ ኢትዮጵያ በተለያዩ የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ላይ መሳተፏን በማንሳት ለአህጉሪቱ ያላት ጥቅም ከፍ ያለ መሆኑን ፈረንሳት እንድትረዳም ተጠይቃለች ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ 5ተኛዋ የፈረንሳይ ትልቅ ገበያ ስትሆን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ደግሞ ሁለተኛው ትልቁ የንግድ ትርፍ የሚገኝባት ናት።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት በመጋቢት 2019 የባህር ሀይል ማዘመንን ጨምሮ ወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በዚህም ከፈረንሳይ ወደ ኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲሁም ከኢትዮጵያም ወደ ፈረንሳይ በተመሳሳይ ወታደሮችን ለመላክ እና በጅቡቲ ሰፍረዉ የሚገኙ የፈረንሳይ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ እንደሚችሉም በወቅቱ ተገልጿል፡፡
ይሁንና የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ወታደራዊ ስምምነቱ ከተፈረመ ከአንድ ዓመት በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ስምምነቱ ሳይተገበር እንደቆየ ተገልጻል።