ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ  አባል ለመሆን የመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ

ከ24 ዓመት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ትስስር ለማሳለጥ የተቋቋመው የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ጥምረት በየጊዜው አዳዲስ አባላትን በመሳብ ላይ ይገኛል።

ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ከአንድ ዓመት በፊት ይህን ጥምረት ለመቀላቀል በይፋ ከጠየቀች በኋላ ባሳለፍነው ሕዳር ወር ጀምሮ አባል መሆኗ ይታወሳል፡፡

ጥምረቱም የመቋዲሾን ጥያቄ ለመመለስ ባለሙያዎቹን አሰማርቶ የተለያዩ ግምገማዎችን ሲያደርግ ቆይቶ ሶማሊያን ስምንተኛዋ አባል ሀገር አድርጎ መቀበሉን በወቅቱ አስታውቋል።

ዋና መቀመጫውን አሩሻ ታንዛኒያ ያደረገው ይህ የኢኮኖሚ ጥምረት በቀጣይ በሚያደርገው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን በይፋ በአባልነት እንደሚቀበል ይጠበቃል።

ዋና ጸሀፊው አክለውም “የጥምረቱ ቀጣይ አባል ሀገር ኢትዮጵያ ልትሆን ትችላለች፣ ኢትዮጵያ አባል የመሆን ፍላጎትም አሳይታለች” ሲሉ ተናግረውም ነበር፡፡

የህብረቱ ዋና ፀሐፊ የሆኑት ፔኒና ማንሎንዛ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብን በአባልነት ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ እየተገመገመ እንደሆነ እና የሁለትዮሽ ዉይይቱ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርብ የህብረቱ አባል እንደምትሆን የተናገሩት ዋና ጸሃፊው ከኢትዮጵያ አባል መሆን ጋር ተያይዞ የኢኤሲ አጋር ሃገራት የህብረቱ የገንዘብ ነክ መመሪያዎችን ባከበረ መልኩ በዚህ ዓመት መጨረሻ የጋራ መገበያያ ገንዘብ እና ጠቃሚ የሆኑ ፖሊሲዎችን በጋራ ለመቅረፅ መፍትሔ በመፈለግ ላይ ናቸዉም ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ የ300 ሚሊዮን ህዝብ መገበያያ መድረክ ሲሆን ኢትዮጵያ አባል ከሆነች የአባል ሀገራቱን ቁጥር ወደ ዘጠኝ የግብይት መጠኑንም ከ400 ሚሊዮን በላይ በማድረስ በአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ የኢኮኖሚ ትስስር ወደ መሆን እንደሚያሸጋግረውም ዋና ጸሀፊው ጠቅሰዋል።

ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን ነባር አባል ሀገራት ሲሆኑ ሶማሊያም ካሳለፍነው ሕዳር ወር ጀምሮ ስምንተኛዋ አባል ሀገር ሆናለች።

በአጠቃላይ ይህን ጥምረት የ700 ሚሊዮን ህዝብ መገበያያ መድረክ የማድረግ ግብ የተቀመጠ ሲሆን የአባል ሀገራቱን የእርስ በርስ ንግድ ልውውጥ ማፋጠን ደግሞ ዋነኛ እቅዱ መሆኑ ተገልጿል።

የአባል ሀገራቱን እርስ በርስ ንግድ ልውውጥ ሊያሳድግ የሚችሉ የባቡር፣ አየር፣ ባህር እና መንገድ ትራንስፖርት ትስስርን ማጎልበት ላይ ያተኩራልም ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *