ኢትዮጵያ ለታንዛንያ 400 ሜጋዋት ሀይል ለመሸጥ ተስማማች

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት በታንዛንያ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዳሬሰላም ቆይታቸው የአቪዬሽን እና ኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ ስምምነት ከፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሐሰን መንግስት ጋር መፈጸማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በሰጡት ሳምንታዊ የዲፕሎማሲ መግለጫ ለይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለታንዛንያ 400 ሜጋዋት ሀይል ለመሸጥ ስምምነት ፈጽማለች ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል በተያዘው ዓመት ከሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገራት ከተሸጠ የኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ 30 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ሶስት ሺህ ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ 182 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዷም ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ የኤሌክትሪክ ሀይል በመሸጥ ላይ ትገኛለች፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥም ለጎረቤት ሀገራት ከሸጠችው የኤሌክትሪክ ሽያጭ 66 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 47 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የፌደራል ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል።

ከኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ የተገኘው ገቢ የቀነሰው በእርስርስ ጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳን የተጠቀመችበትን 70 ሚሊዮን ዶላር እዳ መክፈል ባለመቻሏ ነው ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት ለመሸጥ አቅዳ እየሰራች ነው የተባለ ሲሆን ከታንዛኒያ ጋር ሲደረጉ የነበሩት ድርድሮች መጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡

ከታንዛኒያ በተጨማሪም ለደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የኤሌክትሪክ ሀይል ለመሸጥ የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል መግለጹ ይታወሳል፡፡

የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት የሚያገኙ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር 52 በመቶዎቹ ብቻ ሲሆኑ የሀገር ውስጥ ፈላጎት ሳይሟላ ሀይል ለምን ወደ ጎረቤት ሀገራት ይላካል የሚሉ ወቀሳዎች በመንግስት ላይ እየተሰሙ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በበኩሉ ሀይል ወደ ጎረቤት ሀገራት የምልከው ስራዎች በሚቆሙባቸው ሰዓታት በተለይም ሌሊት ላይ ነው ያለ ሲሆን ሽያጩ መንግስት የገጠመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት ሲባልም ነው ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሀይል እና አቪዬሽን ዲፕሎማሲ እያካሄደች መሆኗን የገለጸች ሲሆን በተለይም የአውሮፕላን አብራሪዎች፣ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እና አቪዬሽን ባለሙዎች ስልጠና ለጎረቤት ሀገራት በመስጠት ላይ እንደምትገኝ አስታውቃለች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *