ጦርነት እና የማህበራዊ መረዳጃ ተቋማት ስብራት በትግራይ

በሀገራችን ኢትዮጵያ ተሰባስቦ ተረዳድዶና ተደጋግፎ መኖር በአጠቃላይ ማህበራዊ ሕይወት አንዱ የሕይወት ዑደት ነው።  ታዲያ ይህ የመረዳዳት ሒደት ደስታን ሐዘንን እንዲሁም የጤና እክልን መሠረት በማድረግ የሚከወን ነው በተለይም እድር እና እቁብን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የሚባሉ እና ማህበረሰቡ ጠብቆና አክብሮ የያዛቸው መረዳጃ እና መደጋገፊያ ሕብረቶችናቸው።

ታዲያ እነዚህ ሕብረቶች በአንድም በሌላም መልኩ እክል ሲገጥማቸው አሊያም የመፍረስ አደጋ ሲጋረጥባቸው ለመታደግ ጊዜ የሚፈጅ እና አስቸጋሪ ይሆናል።

በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ከዛም በፊት በነበረው የኮሮና ወረርሺኝ እንዲህ ያሉ መረዳጃ ማህበራትን ለማጥፋት አሊያም ለማቀዝቀዝ ዋነኛ ምክንያቶች ሆነዋል።

በመቀሌ ከተማ የሚገኝ ትልቅ እድር ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ለተኪዳን በነዚህ ሁለት አጋጣሚዎች የተፈጠረውን የእድሩን ከፍተኛ መቀዛቀዝ ሲገልጹ የኮሮና ወረርሺኝም ሆነ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት እድሩ ለሐዘንም ሆነ ለደስታ ፈጥኖ ደራሽ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ነገር ግን በኮሮናው ወቅት መሰባሰብና መገናኘት የማይፈቀድ በመሆኑ ሁሉም በየቤቱ የተቀመጠበትና እድሩም እምብዛም እንደማይሠራበት አልፎም እየተረሳ እንደነበር እና ወረርሺኙ ስርጭት መቀነስ በጀመረበት ጊዜ ጥቂት መነሳሳቶች ታይተው በየወሩ ገንዘብ ይሰበሰብ ነበር በኋላ ላይ ግን ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ እድርና ማህበራዊ ኑሮ ተቋርጦ እንደነበርም እኝህ እናት ተናግረዋል።

ወ/ሮ ለተኪዳን ከጦርነት በኋላ ስላለው ሁኔታ ሲያብራሩ እጃቸው ላይ ምንም ባለመኖሩ ማህበሩን ማስቀጠል ከብዷቸዋል ። ያቋቋማቸው የነበረውም ንብረት በሙሉ ወድሟል፣ ይህ በመሆኑም በአካባቢው ላይ ሁለት ሐዘን ቢገጥም እጣ እያወጡ ለአንዱ መገልገያ እቃ እንዲሰጥ በማድረግ በችግር እንደሚያሳልፉ ለኢትዮ ነጋሪ አብራርተዋል።

በተለይም ደግሞ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው እና ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት የሞቱ ሰዎች መርዶ በተረዳበት ወቅት ሐዘን በሁሉም ቤት ሲገባ የእድርአ ና መሰል ማህበራዊ መረዳጃ ተቋማት ጥቅም ምንም ሆኗል ብለዋል፡፡

በሁሉም ቤት ሐዘን በመግባቱ እና መገልገያ እቃዎችም በመውደማቸው የትኛው አግዘው የትኛውን መተው እንደሚችሉ ግራ በመጋባታቸው ማህበራዊ ሕይወቱ ሊቆም ነው? የሚል ስጋት ውስጥ  ገብተው እንደነበርም ገልጸዋል።

ይህ እንዳለ ሆኖ አሁንም በጦርነቱ የሞቱ ሰዎች መርዶ አሁንም የቀጠለ መሆኑ የእድሮችን ጥቅም መና ማስቀሩ ተገልጿል፡፡

ሰዎች ሐዘናቸውን እና ችግራቸውን በጋራ ሲወጡባቸው የቆዩ ማህበራዊ ተቋማት መዳከምን አስመልክቶ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳድር ምን ድጋፍ እያደረገ ነው ስንል ጠይቀናል፡፡

የትግራይ ባህልና ቱሪዝም የባህል ኢንዱስትሪ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት ክበብ ለኢትዮ ነጋሪ በሰጡት ምላሽ ከጦርነቱ በፊት የትግራይ ሕዝብ የሚታወቅ ማህበራዊ የሆኑ እሴቶች አሉት ነገር ግን እነዚህ እሴቶች በጦርነቱ ሰአት ሙሉ በሙሉ ተቋርጠው የነበሩ ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ለማስቀጠል የሰው ልጅ በሕይወት መቆየት ያለበት በመሆኑ ተበታትኖና ራሱን ለማቆየት የሚጥርበት ሰአት በመሆኑ ማህበራዊ እሴቶችን ለማስቀጠል ያስባል ወይም ይሞክራል ተብሎ የሚጠበቅ አለመሆኑን የገለጹት ባለሙያው እንደ ሕዝብ አብሮ ለመጓዝና ለመቆየት እነዚህ ማህበራዊ እሴቶች አስፈላጊ እንደመሆናቸው መቋረጣቸው ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስ መፍጠራቸውን አንስተዋል።

ለዚህ መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ማህበራቱን መልሶ የማቋቋምና የማደራቸት ሥራ በቀዳሚነት ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸው እነዚህን ለማስቀጠል ደግሞ ከኢኮኖሚ ጫና ወጥቶ ሥራ መሥራትና ገንዘብ ማግኘት ግድ መሆኑንም ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህ ሲባል የትግራይ ቱሪዝም ቢሮ የልማት ተቋም በመሆኑ ማህበረሰቡን በማደራጀት የዕደ ጥበባትም ሆነ የጉብኝት ሥራዎች በአጠቃላይ ከቱሪዝም ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እንዲሰሩ በማድረግ እንዲሁም በማሰልጠን እና በማደራጀት ሒደት ላይ እንዳለ ኃላፊው ገልጸዋል።

ይሁንና ቢሮው ከዚህ ቀደም ሐዘን እንደደረሰባቸው ሰዎች አይነት የእርዳታ እና የማጽናናት ሥራ ለመሥራት የሚሆን አቅም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የቆየው ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ ከተማ የሰላም ስምምነት መፈረሙ አይዘነጋም፡፡

ይህን ስምምነት ተከትሎ ጦርነት የቆመ ሲሆን ተቋርጠው የነበሩ የግል እና መንግስታዊ ተቋማት ወደ ቀድሞ አገልግሎት ተመልሰዋል፡፡

ይሁንና የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ አለመተግበሩን የክልሉ ጊዜየዊ አስተዳድር እና የፌደራል መንግስት የተናገሩ ሲሆን ቀሪ ስምምነቶችን በቀጣይ እንደሚተገብሩ አስታውቀዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *