በአዲስ አበባ አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ ባለመኖሩ የሆቴሎች ገቢ እየቀነሰ ነው ተባለ

አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ ባለመኖሩ የሆቴሎች ገቢ እየቀነሰ መሆኑን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር እስታወቀ።

ተደራራቢ ችግር እንደፈተነው የሚነገረው የሆቴል ስራ አገልግሎት አሁን ደግሞ የተረጋጋ ሰላም ባለመኖሩ ከአገልግሎቱ እየወጡ የሚገኙ ድርጅቶች መኖራቸው ታውቋል።

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስቴር ሰለሞን ኮቪድ19 ካደረሰው ጉዳት ያላገገሙ ሆቴሎች አሁን ደግሞ በፀጥታ ችግር ምክንያት ከውጭ የሚገቡ ደንበኞቻቸውን እንደልብ ማግኘት አልቻሉም ብለዋል።

ለተከታታይ ዓመታት የዘለቀው የፀጥታ ችግር አሁንም መቀጠሉ በኮከብ ደረጃ ያሉ ሆቴሎች ገቢያቸውን በሀገር ውስጥ ደንበኞች ብቻ መሸፈን አዳጋች እንዳደረገባቸውም ገልፀዋል።

በኮቪድ 19 ወቅት ሆቴሎች ሰራተኞችን እንዳይበትኑና ለአንዳንድ ወጪዎች እስከ 5 በመቶ የወለድ ምጣኔ ብድር ማግኘታቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቷ፥ አሁን ላይ ይህ ድጋፍ መቅረቱን አስረድተዋል ሲል አራዳ ኤፍኤም ዘግቧል።

የሆቴሎች ገቢ እንደወትሮው አለመሆኑን ተከትሎ ለብሔራዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ ማሻሻያ እና ብድር የመክፍያ ጊዜ ገደብ እንዲራዘም ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የሆቴል እና ቱሪዝም አሠሪዎች ፌዴሬሽን ከሶስት ወራት በፊት እንደገለጸው በኢትዮጵያ የሆቴል እና ቱሪዝም ስራ በየጊዜው እየተዳከመ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት ለቪኦኤ እንዳሉት የሆቴል እና ቱሪዝም ቢዝነስ በዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ወደ ቀድሞ አቋሙ ተመልሷል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያም የሆቴል ኢንዱስትሪ ከኮሮና ቫይረስ ጉዳት እንዲያገግም ለመንግስት በቀረቡለት ምክረ ሀሳቦች መሰረት እርምጃ መውሰዱ ዘርፉን ከባሰ ጉዳት ታድጎታል ብለዋል።

የኮቪድ ፕሮቶኮል በሚል ወደ ስራ የተተገበረው አሰራር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ሆቴሎችን ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረጉን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ይሁንና በኢትዮጵያ ግን በየጊዜው እየተዳከመ እና በርካታ የሆቴል ቢዝነስ ባለሀብቶች እና ባለሙያዎች ወደ ሌላ ቢዝነስ እየገቡ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት የሆቴል ኢንዱስትሪውን ጎድቶት ቆይቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሁን ደግሞ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ጦርነት እና የጸጥታ ችግር ተጨማሪ ጉዳት በማድረስ ላይ ነውም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ይህ ሁሉ ችግር ባለበት ሁኔታ ባንኮች የሆቴል ባለቤቶች የወሰዱትን ብድር እንዲከፍሉ ጫና በማድረግ ላይ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡

መንግስት የሆቴል ኢንዱስትሪው ወደ ተባባሰ ችግር ከመግባቱ በፊት የባንኮችን የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙ ግፊት እንዲያደርግም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል፡፡

ባንኮች ለሆቴል ኢንዱስትሪ የሚሰጡት ብድር የመክፈያ ጊዜ አጭር መሆኑ፣ በጦርነቱ ሆቴሎች ኢላማ መደረጋቸው እና በጦርነቱ ምክንያት ሆቴሎች ከስራ ውጪ መሆናቸው ዘርፉን ክፉኛ እየጎዱት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ እድገት ጥሩ የሚባል ነው የሚሉት ፕሬዘዳንቱ አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች ግንባታቸው መቆሙን በአንድ ዓመት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።

እንደ ፍትህ ወልደሰንበት ገለጻ “የነዚህ ሆቴሎች ግንባታ የቆመው በውጭ ምንዛሬ እና በባለሃብቶች ፍላጎት ማጣት ምክንያት ነው”።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *