በኢትዮጵያ ግዙፉ የድንጋይ ከሰል ማጣሪያ ፋብሪካ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ተባለ

በደቡብ ኢትዮጵያ ዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ በ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ፋብሪካ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ተገልጿል።

የከሰል ማዕድን አምራቹ ኢቲ ማይኒንግ ፋብሪካ እንደሚሰኝ ሲገለፅ ፋብሪካው 150 ቶን ከሰል በሰዓት የማምረት አቅምና የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን 75 በመቶ የድንጋይ ከሰል ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል ተብሏል።

የፋብሪካው ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጅነር በላይ አሰፋ የኢትዮጵያ የታጠበ ከሰል ፍላጎት ሀገሪቱ በዓመቱ በአማካይ 400 ሚሊዮን ዶላር እያሳጣት መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ ፋብሪካ ከሁለት ዓመት በፊት ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ ሥራው እየተጠናቀቀ በመሆኑ በፋብሪካው የሚሠሩ ቋሚ ሠራተኞች ሥልጠና እየተሰጠና የሙከራ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተመርቆ ሥራ ይጀምራል ተብሏል።

ይህ የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ ከሁለት ዓመት በፊት የቀድሞው የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ ያስጀመሩት ሲሆን አሁን በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

ፋብሪካው ስራ ሲጀምር በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ ይገነባል ቢባልም አሁን ግን ወጪው ወደ አምስት ቢሊዮን ብር አሻቅቧል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ ባሳለፍነው መስከረም በዓመት እስከ 2.1 ሚሊዮን ቶን የታጠበ የድንጋይ ከሰል ማምረት ይችላል የተባለለት ፋብሪካ ተገንበቶ ስራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

ፋብሪካው የተገነባው ዮ ሆልዲንግ ንግድ እና ማኑፋክቸሪንግ በተባለ የሀገር ቤት ኩባንያ ሲሆን የድንጋይ ከሰል በማምረትና በማቀነባበር ሒደቱ ደግሞ ከሁለት የህንድ ኩባንያዎች ጋር በትብብር ይሰራል ተብሎም ነበር፡፡

በሀገር ቤት ለሚገኙ ለሲሚንቶ፣ ለብረት፣ ለወረቀት፣ ለሴራሚክና ለሌሎች መሰል ምርት ለሚያመርቱ ድርጅቶች የታጠበ የከሰል ድንጋይ ግብዓት እንደሚያቀርብ የፋብሪካው የስራ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካኝ እስከ 1 ሚሊዮን ቶን የሚደርስ የታጠበ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ሀገራት በማስገባት ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የድንጋይ ከሰል ፍላጎት 2.2 ቢሊዮን ቶን ይደርሳል የተባለ ሲሆን ዮ ሆልዲንግ ፋብሪካ በሰዓት 150 እንዲሁም በአመት 1 ሚሊዮን ቶን የታጠበ የድንጋይ ከሰል እንደሚያመርት በወቅቱ ተገልጾም ነበር፡፡

ከአዲስ አበባ በ400 ኪ.ሜ ርቀት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተገነባው ይህ ፋብሪካ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል የተባለ ሲሆን  በጸጥታ እና ግብዓት ችግሮች ምክንያት የታሰበውን ያህል እያመረተ አይደለም፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *