በጣልያን-አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ይህችን አውሮፕላን መረከባቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት “ፀሐይ” አውሮፕላንን ከጣልያን መንግሥት በይፋ መረከባቸውን አስታውቀዋል።
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኔ ላለፈው አንድ አመት የአውሮፕላኑን መመለስ ስራ እንዳገዙም ተገልጿል።
“ፀሐይ” እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1935 ዓ.ም በጀርመናዊው ኢንጂነር እና የንጉሱ ፓይለት ሄር ሉድዊግ ዌበር ብሎም በወቅቱ በነበሩ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ትብብር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መሰራቷ ይታወሳል።
ጣልያን ኢትዮጵያ ቅኝ ለመግዛት ሁለት ጊዜ የሞከረች ቢሆንም የመጀመሪያው ሙከራ በ1880ዎቹ በኢትዮጵያዊያን አርበኞች ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በኢትዮጵያዊያን አርበኞች የተባረረችው ጣልያን ሁለተኛውን የቅኝ ግዛት ሙከራዋን በ1927 ያደረገች ሲሆን ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ከአምስት ዓመታት ብርቱ ትግል በኋላ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
ጣልየን በኢትዮጵያ በቆየችባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ የአክሱም ሀውልትን ጨምሮ በርካታ ቅርሶችን ከኢትዮጵያ ዘርፋ ወደ ሮም የወሰደች ቢሆንም የወሰደቻቸውን ቀርሶች ቀስ በቀስ በመመለስ ላይ ትገኛለች፡፡
ከጣልያን በተጨማሪም ብሪታንያም የኢትዮጵያን ቅርሶች የዘረፈች ሲሆን ኢትዮጵያም የተዘረፉ ቅርሶቿን በማስመለስ ላይ ስትሆን ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የተለያዩ የኢትዮጵያ ቅርሶች በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ ተመልሰዋል፡፡
በ1868 በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት በብሪታንያ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች መመለሳቸውን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡
ከተመለሱት ቅርሶች መካከል በ1868 ዓ.ም ከመቅደላ የተዘረፈ የመድሃኒያለም ታቦት፣ የልኡል አለማየሁ የጸጉር ዘለላ፣ ከብር የተሰሩና በነሃስ የተለበጡ ሦስት ዋንጫዎች እንዲሁም በዘመኑ ጦርነት ላይ የዋለ የጦር ጋሻ እንደሚገኙበት ገልጿል፡፡
ለንደን በሚገኘው የአቴናየም ክለብ በተካሄደው የቅርሶቹ ርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ፤ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልኡካን ቡድን፣ የብሄራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ተወካይ፣ የብሪታኒያ ፓርላማ አባላት፣ ቅርሶቹን ለማሰመለስ የተባበሩ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይም አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፤ የተመለሱት የተለያዩ ቅርሶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖት፣ ታሪክና ባህላዊ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሀብቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አሳዛኝ በሆነው የመቅደላ ጦርነት ምክንያት የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች እስከአሁን አለመመለሳቸው በመላው ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ፈጥሮ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
“እነዚህ ቅርሶች እንደ ቀላል ቁስ የሚታዩ ሳይሆኑ የአንድ ጥንታዊት አገር የታሪክ፣ የባህልና የማንነት መገለጫዎች ናቸው” ብለዋል፡፡
አምባሳደር ተፈሪ አክለውም፤ ኤምባሲው ከመቅደላና ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘርፈው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የተጋዙ ሌሎች ተጨማሪ ቅርሶች እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም ያልተመለሱ ተጨማሪ ቅርሶች በተለያዩ ሀገራት እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን ቅርሶቹን ለማስመለስ ተጨማሪ ግፊት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
ብሪታንያ ከሁለት ዓመት በፊት የአጻ ቴዎድሮስን ጸጉር እና ታቦታት ለኢትዮጵያ መመለሷ ይታወሳል፡፡