የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወይዘሪት ፍሬህይወት የ2016 ዓ.ም የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡
ተቋሙ በስድስት ወሩ በመላው ሀገሪቱ 232 አዳዲስ የሞባይል ኔትወርክ ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብሏል።
ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ተጨማሪ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን አዲስ የሞባይል ኔትወርክ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል መሰረተ ልማት መገንባቱን የገለጸ ሲሆን የድርጅቱ አጠቃይ ደንበኞች ቁጥርም 81 ሚሊዮን እንደደረሱ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በግማሽ ዓመቱ ውስጥ በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች 41 አዲስ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋልም ተብሏል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌኮም ደንበኞች ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛው ተቋም ሲሆን ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለገባው ሳፋሪኮም የቴሌኮም ኩባንያ ጋር ብርቱ ፉክክር እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 43 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ ሲያገኝ ከዚህ ውስጥ 11 ቢሊዮን የተጣራ ትርፍ 18 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለመንግስት ግብር እንደተከፈለ ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ባሳለፍነው ዓመት ያገኘው የተጣራ ትርፍ 8 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን የዘንድሮው ገቢ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ14 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
ሙሉ ለሙሉ የመንግስት ንብረት የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት ዓመት ከአጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎቶች 90 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱ ይታወሳል።
ድርጅቱ በ2016 በጀት ዓመት 13 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት የተቋሙን አጠቃላይ ደንበኞች ቁጥር ወደ 92 ሚሊዮን የማድረስ ውጥን እንዳለውም የኢትዮ ቴሌሎም ስራ አስፈጻሚ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከመንግስታዊው ኢትዮቴሌኮም እና በቅርቡ ገበያውን ከተቀላቀለው ከሳፋሪኮም በተጨማሪ ሦስተኛ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ስራ እንዲጀምር ፈቃድ ለመስጠት ገበያውን እየገመገመች የቆየች ሲሆን በቅርቡ የገበያው ሁኔታ የታሰበውን ያህል አመርቂ ባለመሆኑ ሐደቱ መቋረጡ ይታወሳል።
ከዚህ ጎን ለጎን ከኢትዮቴሌኮም ከግማሽ ያነሰ ድርሻ ለመሸጥም እየጣረች ሲሆን የፈረንሳዩ የቴሌኮም ኩባንያ ኦሬንጅ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት ካሳዩት ዓለምአቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነበር።
ይሁንና ይህ ኩባንያ ከኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ለመግዛት የነበረውን ፍላጎት ማቋረጡን ያሳወቀ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ችግሮች እንደሆኑ ከሁለት ወራት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ኦሬንጅ ግሩፕ በጉዳዩ ላይ ትንተና ከሠራ በኋላ “ስትራቴጂያችንን በፍጥነት ለመተግበር እንዲሁም ለኩባንያችን እሴትን በሚያስገኝ መልኩ ፕሮጄክቱን ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንደሌሉ አምነናል” ብሏል።