የአፍሪካ ልማት ባንክ ከሁለት ወር በፊት በአዲስ አበባ ያሉ ሁለት የባንኩ ሰራተኞች በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች ድብደባ፣ እስር እና እንግልት እንደደረሰባቸው አስታውቆ ነበር።
ባንኩ እንዳለው ሁለት ሰራተኞቹ የቬና የዲልሎማሲ ጥበቃ ስምምነትን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ቢሮ አስተናጋጅ ሀገራት ስምምነትን የጣሰ ክስተት በኢትዮጵያ መፈጸሙንም ገልጿል።
የተፈጠረውን ክስተት ለኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ ማመልከቱን የሚገልጸው የአፍሪካ ልማት ባንክ ጉዳዩ መፈጸም እንደሌለበት፣ ህግ መጣሱን እና ጉዳዩ ተመርምሮ እርምጃ እንደሚወሰድ በኢትዮጵያ በኩል ቃል ተገብቶልኛል ሲልም በወቅቱ አስታውቆ ነበር፡፡
ባንኩ አሁን ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል በገባው መሰረት በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዳልወሰደ እና ጉዳዩ ስለመመርመሩ መረጃ እንዳልሰጠው ገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም ባንኩ የኢትዮጵያ ቢሮውን ሊዘጋ እና ሰራተኞቹንም ወደ ሌላ ሀገራት እንደሚያዘዋውር አስታወቆም ነበር፡፡
ባንኩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ ያስወጣቸውን ሰራተኞች ለመመለስ መወሰኑን እና በአዲ አበባ ያለውን ቢሮ ዳግም ሊከፍት መሆኑን አስታውቋል፡፡
ባንኩ የኢትዮጵያ ቢሮውን የሚከፍተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአፍሪካ ልማት ባንክን ይቅርታ በመጠየቃቸው እንደሆነ በመግለጫው ላይ ገልጿል፡፡
ባንኩ እንደገለጸው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት የደህንነት ዋስትና ካገኘ በኋላ መደበኛ አገልግሎቱን እጀምራለሁ ብሏል፡፡
ባለፈው ወር በባንኩ ፕሬዝደንት አኪንውሚ አደሲና እና በጠቅላይ ማኒስትር ዐቢይ አህመድ መካከል በተካሄደው ውይይት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባንኩን ይቅርታ መጠየቃቸውን እና ለባንኩ ሰራተኞች የደህንነት ዋስተና መስጠታቸውን መግለጫው ጠቅሷል።
መግለጫው አክሎም ለባንኩ ሊተላለፍ በነበረው ስድስት ሚሊዮን ዶላር ጉዳይ ለሚደረግ ምርመራ ለመተባበር መንግስት ቁርጠኛ ሆኗል ብሏል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ በፈረንጆቹ 1963 በሱዳን ካርቱም በተካሄደ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተቋሙ እንዲመሰረት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የተቋቋመ አፍሪካዊ ተቋም ነው።
ባንኩ በአዲስ አበባ ያለውን የኢትዮጵያ ቅርንጫፉን በ1967 የከፈተ ሲሆን በኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ገንዘብ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡