የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሱ-30 የጦር ጄቶች መታጠቁን ገለጸ

የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዘመናዊ የሆነውን የመጀመሪያ ዙር የsu-30 ተዋጊ ጀቶችንና የስትራቴጂክ ሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላኖች መረከቡን ተገለጸ።

በርክክቡ ላይ የተገኙት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፤ በዓለማችን ላይ ተመራጭ የሆኑትን የsu-30 እና የስትራቴጂክ ሰው አልባ አውሮፕላን ባለቤት መሆናችን በሀገራችን ላይ ሊቃጡ የሚሞከሩ ጥቃቶችን ለማክሸፍ ወሳኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የ5ኛ ትውልድ አካል የሆኑት ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖችና የስትራቴጂክ ሰው አልባ አውሮፕላኖች አየር ሀይሉን የማዘመን አንዱ አካል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ሊከላከሉ የሚችሉ ዘመናዊ የውጊያ ትጥቆችን የመታጠቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኤታማዦር ሹሙ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ሀይል “በአፍሪካ በውጊያ አቅሙ፣ በጀግንነቱና በትጥቁ የነበረውን ዝና ዘመኑ በሚጠይቀው መልኩ ለማዘመን” እየተሰሩት ያሉት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ገልጸዋል ሲል መከላከያ ሠራዊት በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡

ዘመን ተሻጋሪ የአየር ሀይል የመገንባት እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋና አዛዡ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፤ አየር ሀይሉ በሰለጠነ የሰው ሀይል፣ በትጥቅና በውጊያ መሰረተ ልማት መጠናከሩን ጠቁመዋል።

ተቋሙ የተረከባቸው ዘመናዊ የጦር ጀቶች በተመሳሳይ ጊዜ በአየርና በምድር ላይ ያለ የጠላት ኢላማን ማውደም የሚችል መሆኑን በመግለጽ ዘመናዊ የሰው አልባ አውሮፕላኖችም የጠላትን ዒላማ የማይስቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ከሶስት ሳምንት በፊት የባህር በር ለማግኘት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር የዲፕሎማሲ መሻከር አጋጥሟል፡፡

ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ነው።

ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

ይህን ተከትሎም የአረብ ሊግ እና ግብጽን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት የሱማሊያ ሉዓላዊነትን እንደሚያከብሩ ስምምነቱን እንደማይደግፉት ተናግረዋል።

 የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የፈረሙት ስምምነት የሚጎዳው ሀገርም ሆነ የሚጥሰው ህግ እንደሌለ ገልጿል።

ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 1991 ጀምሮ ኤርትራ በህዝበ ውሳኔ ሉዓላዊ ሀገር ከሆነችበት ዓመት ጀምሮ ወደብ አልባ ሀገር የሆነች ሲሆን የሕዝብ ፍላጎትን ለመመለስ በሚል አሁን ላይ የባህር በር ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *