ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ወደብ በሊዝ መግዛቷን ገለጸች

በቀይ ባህር ላይ ወደብ እንደሚያስፈልጋት ስትገልጽ የቆየችው ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ወደብ በሊዝ መግዛቷን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

እንደ ጽህፈት ቤቱ መግለጫ ከሆነ የባህር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር ተፈራርማለች፡፡

የባህር በር ሊዝ ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ እንደተፈራረሙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ስምምነት ኢትዮጵያ የቀይ ባህር በር እንዲኖራት ለያዘችው ጥረት ጥሩ መደላደል ሊፈጥር ይችላልም ተብሏል፡፡

ይሁንና የባህር በር ሊዝ ስምምነቱ ለምን ያህል ጊዜ፣ በምን ያህል ገንዘብ እና የስምምነቱ ዝርዝር መረጃ እስካሁን በማንኛውም ወገን ይፋ አልተደረገም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከወራት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት እና ጥያቄውን ለጎረቤት ሀገራት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተከትሎም ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ኤርትራ ጥያቄቀውን ውድቅ አድርገው ምላሽ ሰጥተውም ነበር፡፡

ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በብዙ ጉዳዮች ተባብራ እንደምትሰራ ገልጻ የቀይ ባህር ወደብ የመጠቀም ጥያቄን ግን እንደማትቀበለው አስታውቃለች፡፡

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አሊ ኡመር “የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት- መሬት፣ ባህር እና አየር- ቅዱስ እና ለድርድር የማይቀርቡ ናቸው” ብላም ነበር፡፡

በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ መልስ አትስጥ እንጅ ኤርትራም በውሃ፣ የባህር በር በማግኘት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የሚሰሙ ንግግሮች እንዳልተመቿት ገልጻለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚሰሙ ንግግሮች መብዛታቸውን እና ግራ አጋቢ መሆናቸውን የገለጸችው ኤርትራ የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲጠነቀቁ አሳስባለች።

ጅቡቲም በተመሳሳይ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ውድቅ ያደረገች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ድጋሚ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ በሀይል የባህር በር ጥያቄዋን የመመለስ ፍላጎት እንደሌላት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ መሆኗን ያወጀችው ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በወደብ ጉዳይ ስትሰራ የአሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፊት የነበረው መንግስት ከበርበራ ወደብ የ19 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ገዝቶ የነበረ ቢሆንም ስምምነቱ ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *