በአማራ ክልል የሚገኙ 10 ዩንቨርሲቲዎች በጦርነት ምክንያት ተማሪዎቻቸውን መጥራት አልቻሉም

አማራ ክልል የሚገኙ አስር ዩኒቨርሲቲዎች በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለነባር እንዲሁም አዲስ ለተመደቡ ተማሪዎቻቸው ጥሪ ሳያደርጉ ወራት መቆጠሩ ይታወቃል፡፡

ከአማራ ክልል ውጪ የሚገኙ ዩንቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን ጠርተው በማስተማር ላይ ሲሆኑ በአማራ ክልል ባሉ ዩንቨርስቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች ግን እስካሁን አልተጠሩም።

ይህንን ተከትሎም ተማሪዎቹ ለስነልቦና እና ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን በተደጋጋሚ በማንሳት ላይ ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲዎቹ ጥሪ ሳያደርጉ አራት ወራት በማለፉ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ መግባታቸውንም ይጠቁማሉ፡፡

“ያለ ትምህርት ቁጭ ብለን ወራት አልፈዋል፣ ፍትህ እንሻለን” የሚሉት ተማሪዎቹ፤ ወደ ሌሎች የትምህርት ተቋማት በጊዚያዊነት መዘዋወርን ጨምሮ አማራጭ መፍትሔዎች እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ በአማራ ክልል ያሉ ዩንቨርሲቲዎች በቅርቡ ለተማሪዎቻቸው ጥሪ እንዲያስተላልፉ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) ፤ “ዩኒቨርሲቲዎቹ ለተማሪዎቻቸው ጥሪ እንዲያደርጉ በትምህርት ሚኒስቴር ተነግሯቸዋል” ብለዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ከአስሩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውይይት ማድረጉን የገለፁት ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) ፤ ተቋማቱ በቅርቡ ጥሪ ለማድረግ መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡

ለዚህም “መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል” ያሉ ሲሆን ፤ ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ መንግሥት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ክልሉ እና በክልሉ የሚገኘው ኮማንድ ፖስት በጋራ ይሠራሉ ብለዋል፡፡

የአመራ ዩንቨርሲቲዎች ማህበር ከአንድ ሳምንት በፊት በጋራ ባወጡት መግለጫ ተማሪዎቻቸውን ለመጥራት የደህንነት ችግር እንዳለ ለተማሪዎቹ ጥሪ ቢያቀርቡም ወላጆች ልጆቻቸውን ላይልኩ እንደሚችሉ ስጋት እንዳላቸው ተናግረው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለተማሪዎች ጥሪ ከተደረገ በኋላ ጦርነቱ ቢስፋፋ እና መንገዶች ቢዘጋጉ ተማሪዎች በረሃብ እና ሌሎች ችግሮች ሊጎዱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለባቸውም ተናግረው መንግስት አስተማማኝ ሰላም እስከሚያረጋግጥ ድረስ ለመጥራት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል በቀጠለው ጦርነት ዙሪያ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳለው ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በተለምዶ ፋኖ በመባል ከሚታወቀው አካል ጋር ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡

ይህ ጦርነት በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው ያለ ሲሆን በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች እንዲያመልጡ ተደርጓል የሚለው ኢሰመኮ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎም አሳሳቢ እንደሆኑም አስታውቋል፡፡

የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በተለያዩ የጤና ተቋማት መድረስ የቻሉትን ተጎጂዎች ቁጥር ብቻ መሠረት በማድረግ፣ ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከ200 በላይ የአስገድዶ መድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

የአስገድዶ መደፈር ወንጀሉ ከተፈጸመባቸው አካላት መካከልም የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሴቶች እና የጤና ባለሙያ ሴቶች ጭምር ይገኙበታል ተብሏል።

በክልሉ ያሉ በርካታ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ለወታደራዊ አገልግሎቶች እየዋሉ ነው ያለው ኮሚሽኑ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎች የግልሰቦች ንብረቶች ለውድመት እና ዘረፋ መዳረጋቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል፡፡

በክልሉ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጥም ኢሰመኮ በሪፖርቱ አሳስቧል፡፡

በአማራ ክልል ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በመተዳደር ላይ ይገኛል፡፡

ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ሁሉም ቦታዎች ኢንተርኔት የተዘጋ ሲሆን በርካታ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች ጦርነቱ እንዲቆም፣ የተቋረጠው ኢንተርኔት እንዲለቀቅ እና ድርድር እንዲጀመር ጠይቀዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *