የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኄኖክ ከበደ ከሓላፊነታቸው ተነሱ
የአማራ ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ፕሬዝዳንቱ አቶ ሔኖክ ከበደ ባንኩን ለ460 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ዳርገዋል በሚል ከሀላፊነት አንስቷል፡፡
ባንኩ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው በተጨማሪም የኮርፖሬት አገልግሎት ዋና መኰንኑን አቶ ክንዴ አበበን፣ የአፈጻጸም ድክመት አሳይተዋል በሚል በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር መላኩ ፈንታ ፊርማ ከሓላፊነታቸው አንሥቷል።
የባንኩ ቦርድ ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ኹለቱም ከፍተኛ ሓላፊዎች፣ ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ፣ በየጊዜው በሚሳዩት የሥራ አፈጻጸም ድክመት፣ የባንኩን ስትራቴጂያዊ ግቦች እና ቁልፍ የአፈጻጸም መመዘኛዎችን ማሳካት አልቻሉም ተብሏል፡፡
ባንኩ በ2014/15 ዓ.ም. ከ306 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ለማስመዝገብ ዐቅዶ የነበረ ቢኾንም፣ ብር 460,286,000 ኪሳራ አስመዝግቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ በሌላቸው ሥልጣን ባሳለፉት አስተዳደራዊ ውሳኔ ከ89 ሚሊዮን በላይ ብር እንዲከፈል በማድረግ የባንኩን ካፒታል ከማባከናቸው ባለፈ ባንኩ አጠቃላይ የአፈጻጸም ድክመቶችን እንዲያስመዘገብ ማድረጋቸው ከሀላፊነት እንዲነሱ ዋና ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከሓላፊነታቸው በተነሡት አቶ ኄኖክ አበበ ቦታም የባንኪንግ አገልግሎቶች ከፍተኛ መኰንን በመሆን በመስራት ላይ ያሉት አቶ ጫን ያለው ደምሴ፣ በጊዜዊነት የዋና ሥራ አስፈጻሚነቱን ደርበው እንዲይዙ እንደመደባቸው ታውቋል።
የለንደኑ ኖርዊች ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ ኄኖክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በዳሽን ባንክ ከፍተኛ አመራር በመሆን የሠሩ ሲሆን፤ በ5.9 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ የተመሠረተውን ዐማራ ባንክ የመጀመሪያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ለሁለት ዓመት አገልግለዋል፡፡
በኢትዮጵያ 31 ባንኮች ያሉ ሲሆን አማራ ባንክ በባለአክስዮኖች ብዛት አንደኛ ባንክ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ብዙ ቅርንጫፎችን እና ደንበኞችን ማፍራት ችሎም ነበር፡፡
ሌላኛው የግል ባንክ አሀዱ ባንክ 267 ሚሊዮን ብር እንደከሰረ የገለጸ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 300 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማትረፍ ማቀዱን ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ባንኮች በየዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ በማትረፍ የሚታወቁ ሲሆን ዘንድሮ ግን አማራ እና አሀዱ ባንኮች ባልተለመደ ሁኔታ ኪሳራ ማስመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኪሳራ ያስመዘገቡት ሁለቱ ባንኮችም አዲስ ፕሬዝዳንት ለመሾም እጩዎችን በመፈለግ ላይ ሲሆኑ እስካሁን ይፋ አላደረጉም፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን በሯን ለውጭ ባንኮች ፈቃድ ያልሰጠች ሲሆን ከ2024 ጀምሮ ግን የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ልትፈቅድ እንደምትችል አስታውቃለች፡፡
ብሔራዊ ባንክም የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ነውና የሀገር ውስጥ ባንኮች ራሳቸውን ለውድድር እንዲያዘጋጁ ከአንድ ዓመት በፊት አሳስቧል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲቀሰቀስ ወጋገን ባንክ እና አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንኮች ለኪሳራ ተዳርገው የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ከኪሳራቸው ማገገማቸው ተገልጿል፡፡