ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በሞጆ ከተማ በ50 ሚሊዮን ዶላር የትራክተር ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ ተናግረዋል።
ፋብሪካው ትራክተር የሚገጣጥም ሳይሆን ትራክተሩን ለማምረት የሚያስችሉ ዕቃዎችን የሚያመርት እራሱን የቻለ ፋብሪካ ይሆናልም ብለዋል።
ተገዝተው በሚመጡ ትራክተሮች ብቻ የኢትዮጵያን ግብርና ማዘመን አይቻልም ያሉት አምባሳደር ሱሌይማን፤ ኢትዮጵያ የራሷን “ብራንድ” መትከል ስለሚገባት በሚሊዮን የሚቆጠር ትራክተር የሚያመርት ፋብሪካ መገንባት አለበት ብለን ወደ ተግባር በመግባት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ፋብሪካው የትራክተር ሞተር ጭምር የሚያመርት ስለመሆኑ የጠቀሱ ሲሆን፤ ባሉን ፋብሪካዎችም የመኪና የውስጥ ክፍል “ሻንሲ” የመሥራት አቅም እያዳበርን በመሆኑ፤ ሞተር ማምረት ከቻልን መኪና የማምረት አቅም ላይ እንደሚደረስ ተናግረዋል፡፡
አሁን በመላ ሀገሪቱ በተጨባጭ ያሏት የትራክተሮች ቁጥር ከ100 ሺ እንደማይዘል ግምት እንዳላቸው ያስቀመጡት አምባሳደሩ በቀጣይም ለውጭ ገበያ አዳዲስ ሞዴል ያላቸውን መኪናዎች የማቅረብ ዕቅድ አለው።
እነዚህን ተልዕኮዎቹን ለማሳካትም እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ትራክተር ማምረት እና መገጣጠም ይጀምራል የተባለው ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ባለቤትነት የተያዘ የልማት ድርጅት ነው፡፡
በቀድሞ ስሙ የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እና መካኒካካል ኢንጅነሪንግ በመባል የሚታወቀው ይህ ተቋም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ስሙን ወደ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ቀይሯል፡፡
ይህ ተቋም በአምስት ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ የስኳር እና የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በመያዝ የግንባታ ስምምነት ወስዶ ነበር፡፡
ይሁንና ይህ የመንግሰት የልማት ድርጅት እገነባለሁ በሚል የያዛቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች ከማጠናቀቅ ይልቅ ዋነኛ የሙስና እና የሕዝብ ሀብት ስርቆት ሲፈጸምበት ቆይቷል፡፡
የድርጅቱ የቀድሞ አመራሮች በሙስና ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ይዟቸው የነበሩ የግንባታ ፕሮጀክቶችም ተነጥቀው ለሌሎች የሀገር ውስጥ እና ለውጭ ተቋራጮች ተሰጥተዋል፡፡