መንግስት ብርን የማዳከም ፍላጎት እንደሌለው ገለጸ

ብሔራዊ ባንክ ሪፖርተር ጋዜጣ በሕዳር 23 እትሙ በውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማድረግ መታቀዱን በማስመልከት ያወጣው ዘገባ ሃሰተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡

የሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ ማቀዱን በማስመልከት ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ ሐሰተኛና አሳሳች፣ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት መሆኑን ባንኩ አስታውቋል፡፡

ባንኩ ይህን አስመልክቶ  ባወጣው መግለጫ የሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ በህዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም እትሙ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ከአንድ የፓርላማ አባል ቀረበ ከተባለ አስተያየት ላይ ተነሥቶ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ ማቀዱን በማስመልከት ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ ሐሰተኛና አሳሳች፣ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል ብሏል፡፡

በመሆኑም ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዮን በተመለከተ የቀረበ ዕቅድ ካለመኖሩም ባሻገር እስከ አራት ሰዓት በፈጀው ውይይት ወቅት በብሔራዊ ባንክ የተነገረ ነገር እንደሌለ ህብረተሰቡ ተረድቶ ከዚህ ዐይነት አሳሳች መረጃ እንዲጠበቅ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የሪፖርተር ጋዜጣም በሚቀጥለው እትሙ ይህንኑ የሐሰት ዘገባ እንዲያርም እየጠየቀ በዚህ አሳሳች ዘገባና አሉባልታ ምክንያት በዋጋ ላይ የሚፈጠር ማንኛውም ሰው ሠራሽ ጭማሪ ተቀባይነት እንደማይኖረውና ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግም አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ አንድ ዶላር በባንኮች በኩል 56 ብር በመመንዘር ላይ ሲሆን በጥቁር ገበያ ደግሞ አንድ ዶላር ከ100 እስከ 120 ብር ድረስ ይመነዘራል፡፡

በጦርነት፣ በዋጋ ግሽበት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎች ምክንያቶች የብር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ አንድ ዶላር በ30 ብር ይመነዘር የነበረ ቢሆንም በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ልዩነቱ እየሰፋ ሊመጣ ችሏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *