የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሚሰጠው የብድር ወለድ ላይ ማሻሻያ አደረገ

ባንኩ በግብርና ስራዎች ለተሰማሩ ተበዳሪዎች የብድር ወለድ መጠኑን ከ11 በመቶ ወደ 7 በመቶ ዝቅ ማድረጉን አስታውቋል።

ባንኩ በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎችን ለማበረታታት በሚል ለተበዳሪዎች በሚሰጠው ብድር ላይ ያስከፍል በነበረው ወለድ ምጣኔ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ገልጿል።

የብድር ወለድ ቅናሽ የተደረገው ያ ያልታረሰን የመሬት ሀብት ወደ ስራ ለማስገባት፤ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የበለጠ እንዲበረታቱ ለማድረግ በማሰብ እንደሆነ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት በአነስተኛ፣ መካከለኛና የኮርፖሬት ፕሮጀክት ብድር ለሚጠይቁ ይጠበቅ የነበረው የ11.5 በመቶ የማበደሪያ የወለድ ተመን ወደ 7 በመቶ ዝቅ አድርጓል ብሏል።

ልማት ባንክ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለማሳደግ እና ከውጭ ተመርተው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሚል የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው።

ባንኩ ለደንበኞቹ በሚሰጠው አገልግሎት የሚያገኘውን ዓመታዊ ትርፍ ውስጥ የተወሰነውን ለራሱ ስራ ማከናወኛ እንድጠቀም ይፈቀድልኝ ሲል መንግስትን ጠይቋል።

ባንኩ በሀገሪቱ ያሉ ሰፊ የመልማት አቅም ለመመለስ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ድጋፍ ለማድረግ እና ወደ ውጪ ሀገራት የሚላኩ ምርቶችን በስፋት እንዲመረቱ ለማገዝ መቋቋሙን ከግምት ውስጥ እንዲገባለትም በጥያቄው ላይ ጠቅሷል።

የባንኩ ጥያቄ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ ያገኘ ሲሆን በመሆኑም በየዓመቱ ያገኘውን ትርፍ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ ከሚያደርገው ላይ ሙሉ ለሙሉ አልያም በከፊል ለራሱ እንዲወስድ እንዲፈቀድለት የምክር ቤቱ አባላት ለገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሰጡት ምላሽ መንግስት ልማት ባንክ ከነበረበት ኪሳራ እንዲወጣ ላለፉት አምስት ዓመታት የተበላሸ ብድር እንዲስተካከል፣ የበጀት እጥረቱ እንዲፈታ፣ የአሰራር ማሻሻያዎችን ጨምሮ ብዙ ድጋፎችን ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ልማት ባንክ በቋሚነት ዓመታዊ ትርፉን ለራሱ ስራዎች እንዲያውል የፈቅድ ህግ ሊጸድቅ አይገባም ባንኩ ውጤታማ እንዲሆን ግን ድጋፍ ይደረግለታል ሲሉም ተናግረዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *