በጦርነት በተጎዳችው ትግራይ የ6 ቢሊዮን ብር ብረት ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ እንደሆነ ተገለጸ

በ6 ቢሊዮን ብር ወጪ በኢትዮጵያ እና ቻይና ባለሃብቶች ትብብር የብረታ-ብረት ማምረቻ ኢንዱስትሪ በመቐሌ ከተማ ሊገነባ ነው።

በአስር ወራት ውስጥ የሚገነባው ይህ ኢንዱስትሪ የስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ይፋ ተደርጓል።

በዚህ ወቅት የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የሌጀንድ ብረታብረት ኢንዱስትሪ ሃላፈነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ አስፈጊው ድጋፍ ይደረግለታል ብለዋል።

ሌሎች በግልና በማህበር የተደራጁ ባለሃብቶችም የዚህን የልማት ፕሮጀክት አርአያ ተከትለው በማልማት  ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ መልእክት አስተላልፈዋል።

የብረታብረት ማምረቻው 75 በመቶ በኢትዮጵያዊው ባለሃብት ኢንጅነር ያሬድ ተስፋይ የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው 25 በመቶ ደግሞ በቻይናዊው ባለሃብት ሚስተር ሊ ዮን መሸፈኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሳምሶም ገብረመድህን ገልጸዋል።

የሌጀንድ ብረታ ብረት ማምረቻ ኢንደስትሪ 6ሺህ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል ሲል ተብሏል።

የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ይተባረክ አመሃ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ  ለሌጀንድ ብረታብረት ኢንደስትሪ  አሁን ከተሰጠው የግንባታ ቦታ  ባለፈም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ   ለማድረግ ዝግጁ መሆኑ አረጋግጠዋል።

ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት፣ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ማድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህ ጦርነት ለዓመታት በብድር እና በህዝብ ገንዘብ የተገነቡ መሰረተ ልማተቶችን እንዲወድም ያደረገ ሲሆን በአጠቃላይ የ28 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ በሀገር ላይ እንዳደረሰ ተገልጿል።

ግጭትና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ጠቅላላ ነዋሪዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በጦርነቱ በቀጥታ ተጎድተዋልም ተብሏል።

በዚህ ውስጥ ምክንያትም ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት ወደ ከፋ ድህነት ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።

በዚህ ጦርነት የደረሰው ውድመት ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከውጭ አበዳሪዎች ለኢኮኖሚ ልማት ተበድራ ካልመለሰችው አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ጋር እኩል ሆኗል።

በአጠቃላይ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የገንዘብ ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም ሪፖርት ያስረዳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *