አቦል ቴሌቪዥን ከሰኞ ህዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሁለት አዳዲስ “ሀገርኛ” ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማዎችን ለተመልካቾቹ ላቀርብ ነው ብሏል፡፡
ለተመልካቾች የሚቀርቡት “ቁጭት” የተሰኘው ረጅምና ወጥ ሀገርኛ ተከታታይ ቴሌኖቬላ እና “ዳግማዊ” የተሰኘው በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው ድራማ ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ይዘቶች አቦል ቴሌቪዥን ለደንበኞቹ ምርጥ ወጥ ሀገርኛ ይዘቶችን ለማቅረብ የወጠነውን ጅምር በተግባር የሚያረጋግጡና ቻናሉ የላቁ መዝናኛዎችን ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው።
“ቁጭት” የተሰኘው ሀገርኛ ቴሌኖቬላ ታሪኩ የሚያጠነጥነው በሕይወት ጥቂት ወራት ብቻ እንደሚቀረው ከተነገረው በኋላ የናፈቀውን ልጁን ዮናስን ለማግኘት ፍለጋ በጀመረ አባት ነው፡፡
ድርጊቱ በተስፋ ማጣት እና በድህነት ውስጥ ያለን የሕይወት ውጣውረድም የሚያስቃኝ ሲሆን ዮናስ የአባቱን ህልውና እና ባለጸጋነት ታሪክ ሳያውቅ ሕይወቱ ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ሲወሰድም በአጓጊ ትወናዎች ያሳያል፡፡
በፈጣን ድርጊቶች የተሞላው ይህ የቤተሰብ ድራማ ተመልካቾችን በእጅጉ እንደሚያዝናና ታምኖበታል፡፡ ቁጭት ዘወትር ከሰኞ እስከ አርብ ምሽት ከ2፡30 ሰዓት ጀምሮ በአቦል ቴሌቪዥን በዲኤስቲቪ ቻናል ቁጥር 465 ላይ ይተላለፋል ተብሏል፡፡
በሌላ መልኩ “ዳግማዊ” የተሰኘውና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው ተከታታይ ድራማ ዘወትር ሰኞ ከምሸቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በአቦል ቴሌቪዥን የሚተላለፍ ተገልጿክ፡፡
“ዳግማዊ” በአንድ ወቅት በሀዋሳ ከተማ አጋጥሞ በነበረ እውነተኛ ታሪክ ላይ በተጻፈው ዳግማዊ መጽሐፍ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ሲሆን ስለ ተጨባጭ ፍትህ ሲባል አደጋን ስለተጋፈጠው ወጣት ጠበቃና ጓደኛው የሚተርክ ነው፡፡
የእነርሱ አሳዛኝ፣ ነገር ግን ደፋር ጉዟቸው በመማር ልምድ፣ በፈተናዎች እና አስደንጋጭ ድርጊቶች የተሞላ ሲሆን ይህ እውነተኛ ታሪክም ተመልካቾችን እንደሚያስደንቅ ጥርጥር የለውም። የዳግማዊን የሞራል ልዕልና፣ የወጣትነት እውነትን ፍለጋና ውስብስብ ጉዳዮችንም ይዳስሳል።
የሁለቱን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች አስመልክቶ የዲኤስቲቪ/መልቲቾይስ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ገሊላ ገ/ሚካኤል “አቦል ቴሌቪዥን ምንጊዜም የላቀ የሀገር ውስጥ መዝናኛ ቻናል ለመሆን ቁርጠኛ ነው” ያሉ ሲሆን “በቁጭት እና ዳግማዊ ይዘቶች ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ብዝኃ ባህልና እሴት ለማሳየት ብሎም የኢትዮጵያውያንን የፊልም ጥበብ ባለሙያዎችን ችሎታና ጥልቀት ለታዳሚዎች ለማድረስም እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡
“ቁጭት እና ዳግማዊ የተሰኙት ተከታታይ ድራማዎች ወቅቱን የሚመጥኑ፣ ትኩስ ሀገርኛ ጣእም እና ጥራት ያላቸው ይዘቶች ናቸው፤ ይህም በኤም-ኔት ባለቤትነት በሚንቀሳቀሰው አቦል ቴሌቪዥን አማካኝነት ለተመልካቾቻችን የላቁ ይዘቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየተደረገ ላለው ጥረት አይነተኛ ምሳሌ ናቸው” ብለዋል፡፡