ከ24 ዓመት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ትስስር ለማሳለጥ የተቋቋመው የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ጥምረት በየጊዜው አዳዲስ አባላትን በመሳብ ላይ ይገኛል።
ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ከአንድ ዓመት በፊት ይህን ጥምረት ለመቀላቀል በይፋ መጠየቋ ይታወሳል።
ጥምረቱም የመቋዲሾን ጥያቄ ለመመለስ ባለሙያዎቹን አሰማርቶ የተለያዩ ግምገማዎችን ሲያደርግ ቆይቶ ሶማሊያን ስምንተኛዋ አባል ሀገር አድርጎ እንደሚቀበል አስታውቋል።
ዋና መቀመጫውን አሩሻ ታንዛኒያ ያደረገው ይህ የኢኮኖሚ ጥምረት በሚቀጥለው ሳምንት በሚያደርገው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ሶማሊያን በይፋ በአባልነት እንደሚቀበል ገልጿል።
የጥምረቱ ዋና ጸሀፊ ፒተር ማቱኪ በሞሮኮ ማራካሽ በተካሄደው የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ እንዳሉት “ሶማሊያ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ አባል ትሆናለች” ብለዋል።
ዋና ጸሀፊው አክለውም “የጥምረቱ ቀጣይ አባል ሀገር ኢትዮጵያ ልትሆን ትችላለች፣ ኢትዮጵያ አባል የመሆን ፍላጎትም አሳይታለች” ሲሉ ተናግረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ የ300 ሚሊዮን ህዝብ መገበያያ መድረክ ሲሆን ኢትዮጵያ አባል ከሆነች የአባል ሀገራቱን ቁጥር ወደ ዘጠኝ የግብይት መጠኑንም ከ400 ሚሊዮን በላይ በማድረስ በአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ የኢኮኖሚ ትስስር ወደ መሆን እንደሚያሸጋግረውም ውና ጸሀፊው ጠቅሰዋል።
ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን ነባር አባል ሀገራት ሲሆኑ ሶማሊያም ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ስምንተኛዋ አባል ሀገር ትሆናለች።
በአጠቃላይ ይህን ጥምረት የ700 ሚሊዮን ህዝብ መገበያያ መድረክ የማድረግ ግብ የተቀመጠ ሲሆን የአባል ሀገራቱን የእርስ በርስ ንግድ ልውውጥ ማፋጠን ደግሞ ዋነኛ እቅዱ መሆኑ ተገልጿል።
የአባል ሀገራቱን እርስ በርስ ንግድ ልውውጥ ሊያሳድግ የሚችሉ የባቡር፣ አየር፣ ባህር እና መንገድ ትራንስፖርት ትስስርን ማጎልበት ላይ ያተኩራልም ተብሏል።