በአማራ ክልል ንጹሀን ዜጎች ከፍርድ ውጪ እየተገደሉ መሆኑን ኢሰመኮ ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሚያዝያ ወር 2015 ጀምሮ በአማራ ክልል የሚታየውን የጸጥታ ችግር እንዳሉ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ እንዳለው በክልሉ የነበረው የጸጥታ ችግሩ ወደ ትጥቅ ግጭት ማምራቱን ተከትሎ የንጹሀን ዜጎች ግድያ እና እንግልት ቀጥሏል ብሏል።

በተለይም ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 30/2015 ድረስ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ንጹሃን መሞታቸውን እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አስታውቋል።

“በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ፣ በሰሜን ጎጃም ዞን አዴትና መራዊ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደልጊ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ፣ ሸዋ ሮቢት እና አንጾኪያ ከተሞች እና በአካባቢዎቻቸው በሚገኙ አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች በግጭቱ በርካታ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል ተብላል።

እንዲሁም ለአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች እጅግ አሳሳቢ ናቸው ያለው ኮሚሽኑ፤ ከሐምሌ 24 እስከ ጳጉሜን 04/2015 ድረስ በተለይም በአዴት፣ ደብረማረቆስ፣ በደብረ ታቦር፣ ጅጋ፣ ለሚ፣ ማጀቴ፣ መራዊ፣ መርጦ ለማርያምና ሸዋ ሮቢት ከተሞች በርካታ ከሕግ ውጭ ግድያዎች መፈጸማቸው ተገልጻል።

ግድያዎቹ ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ የተያዙ ሰዎች፣ በግጭቱ ወቅት መንገድ ላይ የተገኙ እና ያልታጠቁ ሰዎች፣ “የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል የተያዙ ሰዎች እንዲሁም የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተላልፈው የተገኙ ሲቪል ሰዎችና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የፋኖ አባላት መሆናቸውንም ጠቁሟል።

ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎችም በኮሚሽኑ እና በአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርዱ የተሟላ ምርመራ ሊደረግበት ይገባል ሲልም አሳስቧል።

ኮሚሽኑ ይህን መግለጫ ይፋ እስካደረገበት ጊዜ ድረስ አደረኩት ባለው ክትትል፤ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች፣ ከሕግ ወይም ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች እና የዘፈቀደ እስር እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው ተብሏል፡፡

ስለሆነም በየትኛውም ወገን የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሲቪል ሰዎችን ወይም የመሠረተ ልማቶችን ዒላማ ከማድረግ ሙሉ በሙሉ እንዲቆጠቡ እንዲሁም፤ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ መከላከል ጨምሮ ለሲቪል ሰዎች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግም ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።

በማናቸውም ኹኔታ ሊገደቡ የማይችሉ መብቶችን በተለይም በሕይወት የመኖር መብት እና ከኢ-ሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት እንዲከበሩም ኮሚሽኑ ጠይቋል።

በንጹሃን ሰዎች ላይ ግድያ በፈጸሙና በዘፈቀደ እስራት ላይ በተሳተፉ አካላት ላይ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም ኢሰመኮ አሳስቧል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *